በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ውጥረትን ለመቀነስ ከሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ መሪዎች ጋር ስብሰባ መታቀዱን የኬንያው ፕሬዚደንት አስታወቁ


በአውሮፓዊያኑ ጥቅምት 2022 የተወሰደው ምስል ፣ አዲስ አበባ ላይ በሳፋሪኮም ስነ ስርዓት ላይ ተሳታፊ የነበሩትን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ያሳያል።
በአውሮፓዊያኑ ጥቅምት 2022 የተወሰደው ምስል ፣ አዲስ አበባ ላይ በሳፋሪኮም ስነ ስርዓት ላይ ተሳታፊ የነበሩትን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ያሳያል።

የሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ መሪዎች የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውጥረቶችን "ለመቀነስ" ስብሰባ ለማድረግ ማቀዳቸውን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ትናንት አርብ አስታውቀዋል።

ሩቶ ይህንን የተናገሩት የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ 24ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤውን ባካሄደበት ታንዛኒያ፣ አሩሻ ባደረጉት ንግግር ነው።


የማህበረሰቡ አዲስ ሊቀመንበር ሩቶ ፣ ስብሰባው የሚደረግበትን ቀን ይፋ አላደረጉም ።ስብሰባው እርግጥ ከሆነ ፣አዲስ አበባ እና ሶማሌላንድ አወዛጋቢውን የመግባቢያ ሰነድ በአውሮፓዊያኑ ጥር 1 ፣2024 ከተፈራረሙ ወዲህ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረግ የመጀመሪያ የፊት ለፊት ስብሰባ ይሆናል።

የሶማሊያ መሪዎች የመግባቢያ ሰነዱ እስካልተሰረዘ ድረስ ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ምንም አይነት ቀጥተኛ ንግግር እንደማይኖር አጽንኦት ሲሰጡ ሰንብተዋል።

ቱርክ ቀደም ሲል ፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ሁለት ስብሰባዎችን በአንካራ ላይ አመቻችታ ነበር ።በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ልዑካኑ ፊት ለፊት ባለመገናኘታቸው ተጨባጭ እድገት ሳይገኝ ቀርቷል። በአውሮፓዊያኑ መስከረም 17 ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ሶስተኛው ዙር ውይይት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።


ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ 8ኛ አባል ሀገር ሆና የተቀላቀለችው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነው።

"የቀጠናችንን ሰላም ለማስጠበቅ ፣ ለቀጠናችን ፀጥታና መረጋጋት መዋለ ነዋይ ለማፍሰስ የጋራ ጥረት (ያሻል) " ፣ በማለት ጥሪ ያቀረቡት ሩቶ ፣ በንግግራቸው ወቅት ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቅ ፣ በቀጠናው የመዋለ ነዋይ ፍሰትን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

"በተጨማሪም ፣ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ውጥረት ለመቀነስ በፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ፣ በራሴ፣ በወንድሜ ሀሰን ሼክ እና በጠቅላይ ሚንስትር አብይ መካከል ምክክር ለማድረግ አቅደናል ።ምክንያቱም የሶማሊያ ደህንነት እና መረጋጋት ፣ ለቀጠናው መረጋጋት ፣ ለንግድ ሰዎች ፣ ለመዋለ ነዋይ አፍሳሾች እና ስራ ፈጣሪዎች እመርታ በእጅጉ አስተዋጽኦ አለው ” ሲሉም አክለዋል።

ኬንያ በደቡብ ሱዳን የሰላም ጥረቶች ውስጥ እየሰራች መሆኗን የተናገሩት ሩቶ ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሌሎች አጋር መንግስታት ጋር እየሰራች መሆኗን እስታውቀዋል።


“የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሶማሊያ መረጋጋት ለቀጠናው ብልጽግና ቁልፍ ሚና አለው " ሲሉ ሩቶ በትናንትናው ዕለት በኤክስ አውታር ላይ አጋርተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG