በፖሊሶች እና በህገወጥ መንገድ ማዕድን በሚቆፍሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረው ፍጥጫ ምክኒያት መውጫ ያጡት ቆፋሪዎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቅ የለበትም ሲሉ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ አሳሰቡ፡፡ ማዕድን ቆፋሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ መውጣት አለባቸው ሲሉ ፕሬዚደንቱ አሳስበዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሰሜን ምዕራብ ክፍለ ግዛት የተራረፈ ወርቅ ፍለጋ በመቶዎች የተቆጠሩ ቆፋሪዎች የተዘጋ ጉድጓድ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የገቡ ሲሆን ፖሊሶች ሲወጡ ለመያዝ ምግብ እና ውሃ እንዳይገባላቸው ከልክለዋል፡፡
ህገወጥ የማዕድን ቁፋሮ ደቡብ አፍሪካን የወረሳት ችግር ሲሆን ባለፉት ሳምንታት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ህገ ወጥ ማዕድን ፈላጊዎች ከማእድን ጉድጓዶች ውስጥ ወጥተዋል፡፡ ሆኖም ባለፈው ሳምንት የሀገሪቱ ፖሊሶች አሁንም ያልወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ምግብ እና ውሃ እንዳይደርሳቸው መደረጉን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነቅፈዋል፡፡
ሁኔታው ብጥብጥ ሊቀሰቅስ የሚችል መሆኑን የተናገሩት ራማፎሳ ፖሊሶች ወንጀለኞችን ሳያመልጡ ለመያዝ የተከተሉት አግባብ ያለው አሰራር ቢሆንም ሰዎቹን ህይወታቸው አደጋ ላይ ሳይወድቅ ከጉድጓዱ ለማስወጣት ፖሊስ ኅላፊነቱን ይወጣል ብለዋል፡፡
ማዕድን ቆፋሪዎቹ የቀሩት ለመውጣት ባለመቻላቸው ይሁን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንደሆን አልታወቀም፡፡
መድረክ / ፎረም