በቅርቡ አዲስ በተሾሙት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ እየተመራ፣ በአዘርባይጃን ዋና ከተማ ባኩ እየተካሄደ ባለው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ በመሳተፍ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከባድ ጉዳት እየደረሰባቸው ላሉ ያላደጉ ሀገራት ለመስጠት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ ወደ 1.3 ትሪሊየን ዶላር ያድጋል ብሎ እንደሚጠብቅ፣ በድርድሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ አቶ ያሬድ አበራ ገልጸዋል።
"የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች ጉባዔ የወቅቱ ሊቀመንበር የኾነችው ኢትዮጵያ ከሌሎች ታዳጊ ሀገራት ሀገራት ጋራ በመሆን የገንዘብ ድጋፉ ስምምነት ላይ እንዲደርስ ጥረት እያደረገች ነው" ያሉት አቶ ያሬድ፣ ከከርሰ ምድር የሚወጣ ኃይል አጠቃቀምን ለመቀነስ እና የዓለምን ሙቀት ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ግን አሁንም አዳጋች መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም. ፓሪስ ላይ በተካሄድው 21ኛው ጉባዔ የዓለም ሀገራት በፈረሙት የፓሪስ ስምምነት የዓለም ሙቀትን 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ለመገድብ ተስማምተው ነበር። ይህንንም ለማሳካት እ.አ.አ በ2030 ሙቀት ማመቅ የሚችሉ የጋዝ አይነቶችን በ43 ከመቶ ለመቀነስ እና በ2050 ዓለምን ከካርበንዳይኦክሳይድ የፀዳ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ባለፉት 40 ዓመታት ባልታየ ድርቅ ሲሰቃይ የነበረው የአፍካ ቀንድ አካባቢ ባለፈው ዓመት የተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ከ1.6 ሚሊየን በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉ አድርጎ የነበረ ሲሆን ከእነዚኽ ውስጥ 396 ሺሕ የሚሆኑት የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አክሽን አጌንስት ሀንገር የተሰኘው በአፍሪካ ቀንድ ረሃብን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ርዳታ ሰጪ መረጃ ያመለክታል።
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያከትለው ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋም መንገዶችን እና ቤቶችን ከማጥለቅለቁ እና ነዋሪዎችን ከማፈናቀሉ በተጨማሪ የውሃ ምንጮች እንዲበቀሉ እንዲሁም የጤና ተቋማት እንዲወድሙ በማድረጉ፣ በክልሉ ለበሽታ ተጋላጭነት ጨምሯል።
በአየርን ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱት እነዚህ ተደራራቢ ጉዳቶችን እያስተናገደች ያለችው ኢትዮጵያ በአየርን ንብረት ለውጥ ተጠቂ ከሆኑ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የጋራ አቋም በመያዝ በዓለም አቀፍ ጉባዔው ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።
/ከአቶ ያሬድ አበራ ጋራ የተደረገውን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።/
መድረክ / ፎረም