በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት በቀጠለበት ሁኔታ፣ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን በማስተዳደር ላይ ባለችው ሶማሊላንድ ዛሬ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በመካሄድ ላይ ነው።
ሶማሊላንድ ከእ.አ.አ 1991 ጀምሮ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን በማስተዳደር ላይ ስትሆን፣ በሽብር ከምትናጠው ሶማሊያ አንጻር የሰላምና መርረጋጋት ደሴት ተደርጋ ትታያለች፡፡ ሆኖም ግን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና አልተሰጣትም።
በሃርጌሳ በመቶ የሚቆጠሩ ድምጽ ሰጪዎች ጎሕ ከመቅደዱ በፊት በድምጽ መስጪያ ጣቢያዎች ተሰልፈው ተስተውለዋል። በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች ሙቀቱ ከማየሉ በፊት በማለዳ ድምጽ ለመስጠት የወጡ ሰዎች ታይተዋል።
የወቅቱ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ፣ ተቀናቃኛቸው አብድራህማን ሞሃመድ እንዲሁም ሌላው ተፎካካሪ ፋይሳል አሊ ዋራቤ በማለዳ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋራ የባሕር በር አጠቃቀምን በተመለከተ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት በመስፈኑ ባልተረጋጋው ቀጠና ሌላ ግጭት እንዳይነሳ ተሰግቷል።
ፕሬዝደንት ቢሂ ኢትዮጵያ በምትኩ ለሶማሊላንድ እውቅና ትሰጣለች ቢሉም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን አላረጋገጠም። የስምምነቱ ዝርዝርም እስከ አሁን ይፋ አልሆነም።
የቢሂ ተቀናቃኞች ስምምነቱን ሲነቅፉ አይስተዋሉም።
ከእ.አ.አ 2017 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የቆዩት ቢሂ፣ በድጋሚ የሚመረጡ ከሆነ ስምምነቱን እንደሚያስቀጥሉ ይናገራሉ።
መድረክ / ፎረም