በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ የድንበር ቁጥጥር ዋና ባለስልጣን እና በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደራቸውን ሾሙ


ፋይል - በፕሬዘዳንት ትራምፕ የድንበር ቁጥጥር ዋና ባለስልጣን አድርገው የሾሟቸው ታም ሆማን በናሹዋ በተካሄደው የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ምሽት የሪፐብሊካን ድግስ ላይ ሲናገሩ፣ ጥር 14 2016 ዓ.ም
ፋይል - በፕሬዘዳንት ትራምፕ የድንበር ቁጥጥር ዋና ባለስልጣን አድርገው የሾሟቸው ታም ሆማን በናሹዋ በተካሄደው የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ምሽት የሪፐብሊካን ድግስ ላይ ሲናገሩ፣ ጥር 14 2016 ዓ.ም

የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ብዛት ያላቸው ፍልሰተኞች እንደሚያባርሩ በምረጡኝ ዘመቻቸው የገቡትን ቃል የሚያስፈጽሙላቸውን ባለስልጣን ሾመዋል።

የድንበር ቁጥጥር ዋና ባለስልጣን "ቦርደር ዛር" ሆነው የተሾሙት በአንድ ወቅት የኢሚግሬሽን ጉዳይ ዋና መሥሪያ ቤት ተጠባባቂ ዳይሬክተራቸው የነበሩት ታም ሆማን ናቸው።

ትረምፕ ትላንት ማታ በትሩዝ ሶሺያል ማህበራዊ መገናኛቸው ባወጡት ጽሁፍ ለድንበሮቻችን ጥበቃ እና ቁጥጥር ከሳቸው የተሻለ ሰው አይገኝም" ብለዋል።

ተመራጩ ፕሬዚደንት በስደተኞች ጉዳይ ሌላው አክራሪ አቋም ያላቸው የሆኑትን ስቲቭን ሚለርን የጽህፈት ቤታቸው የፖሊሲ ጉዳዮች ምክትል ኅላፊ አድርገው እንደሚሾሟቸው የዩናይትድ ስቴትስ የዜና አውታሮች ዘግበዋል።

ትረምፕ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቲትስ ኮንግሬስ ካሏቸው ዋና ዋና ደጋፊዎች አንዷ የሆኑትን የኒው ዮርክ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ኤሊስ ስቴፋኒክን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር እንዲሆኑ ሾመዋቸዋል።

ተመራጩ ፕሬዚደንት ሴኔተር ማርኮ ሩቢዮን የውጪ ጉዳይ ሚንስትራቸው ያደርጓቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ትላንት ሮይተርስ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

የትረምፕም ሆኑ የሴኔተር ሩቢዮ ተወካዮችን አስተያየት ለማግኘት እንዳልቻለ ሮይተርስ አመልክቷል።

የዩናይትድ ስቲትስ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ማይክል ዎልዝን የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪያቸው እንዲሆኑ የጠየቋቸው ሲሆን የቀድሞ የኒውዮርክ የዩናይትድ ስቲትስ ምክር ቤት ተወካይ ሊ ዜልዲንን ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ኅላፊነት መምረጣቸው ተዘግቧል።

የኢሊስ ስተፋኒክ እና የሊ ዜልዲን ሹመት በመወሰኛ ምክር ቤት መጽደቅ ይኖርበታል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG