የኡጋንዳ ወታደራዊ ፍርድ ቤት "በሕግ ወጥ መንገድ ፈንጂ ይዞ በመገኘት እና የሀገር ክህደት በመፈጸም" በተወነጀሉ 16 የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ በትላንትናው እለት የጥፋተኝነት ብይን ማሳለፉን አንድ የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ አስታወቁ። የችሎቱን ውሳኔም ‘አጠያያቂ’ ብለውታል።
አቃቤ ሕግ 16’ቱን የተቃዋሚው ይብሔራዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ አባላት እና እስከአሁን አልተያዙም ያላቸውን ሌሎች ግለሰቦች እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በሕዳር 2020 እና በግንቦት 2021 መካከል ባለው ጊዜ በሃገሪቱ ምርጫ እየተካሄደ ሳለ የተባሉትን ወንጀሎች ‘ፈጽመዋል’ ሲል ነው የከሰሳቸው።
ሻሚም ማሌንዴ የተባሉ የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ "ካሁን ቀደም ወንጀሉን አልፈጸምንም” ሲሉ ክሱን ያስተባበሉት ተከሳሾች አሁን ጥፋተኝነታቸውን አምነዋል የተባለበትን ሁኔታ “አጠያያቂ ነው" ብለውታል።
‘ባቢ ዋይን’ በሚል የመድረክ ስም የሚታወቀው የቀድሞ ድምጻዊ ሮበርት ኪያጉላኒ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል፤ ቡድኑ ጥፋተኛነቱን አምኖ ፕሬዝዳንታዊ ይቅርታ እንዲጠይቅ መገደዱን ተናግሯል። 16ቱ ተከሳሾች አራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩ ሲሆኑ፤ ነገ ረቡዕ ችሎቱ ዘንድ ይቀርባሉ። ጋዜጠኞች ሥነ ስርአቱን እንዳይከታተሉ ታግደዋል።
ምሥራቅ አፍሪቃዊቱ አገር ኡጋንዳ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1986 አንስቶ በዩዌሪ ሙሴቬኒ ስትመራ መቆየቷ ይታወቃል።
መድረክ / ፎረም