በርሊን በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅዷል ተብሎ የተጠረጠረ እና ከእስላማዊ መንግስት ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው የተገለጸው ሊቢያዊ ተጠርጣሪ እሁድ ፍርድቤት እንደሚቀርብ የጀርመን አቃብያነ ህጎች አስታወቁ።
ስሙ ኦማር ኤ. እንደሆነ የተገለጸው ተጠርጣሪ፣ ቅዳሜ ምሽት በቁጥጥር ስር የዋለው፣ ከጀርመን ዋና ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው በርናው ከተማ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ መሆኑን የፌደራል አቃቢያነ ህጎች ቢሮ አመልክቷል።
ቢሮው አክሎ፣ ኦማር ኤ. በርሊን በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ላይ "በጦር መሳሪያ የታገዘ ከፍተኛ ጥቃት ለማድረስ አቅዷል" የሚል ክስ እንደተመሰረተበት አመልክቷል። የእስላማዊ መንግስት ርዕዮተ ዓለም ደጋፊ መሆኑን የገለጸው አቃቤ ህግ፣ ለጥቃቱ ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅትም "ከእስላማዊ መንግስት አባላት ጋር በማህበራዊ ሚዲያ መልዕክት ተለዋውጧል" ብሏል።
በርሊን የሚገኙት የእስራኤል አምባሳደር ሮን ፕሮሶር በኤክስ ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "የሙስሊም ፀረ-ሴማዊነት፣ ትርክት ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ የሽብር ድርጊቶችን የሚያበረታታ እና የሚያነሳሳ ነው" ብለዋል። አክለውም የእስራኤል ኤምባሲዎች "በዲፕሎማሲው ጦር ሜዳ ግንባር ተሰላፊ ናቸው" ሲሉም አመልክተዋል።
የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንችይ ፌዘር በበኩላቸው፣ በጀርመን የሚገኙ አይሁዳውያንን እና የእስራኤል ተቋማትን መጠበቅ "ከምንም በላይ ቅድሚ የምንሰጠው ነው" ያሉ ሲሆን፣ የሕግ አስከባሪ አካላት ማንኛውንም እስላማዊ፣ ፀረ-ሴማዊ እና ፀረ-እስራኤል ጥቃቶችን ለመከላከል ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
መድረክ / ፎረም