እስራኤል በሊባኖስ ዋና ከተማ የሂዝቦላህ "የትዕዛዝ ማዕከል" ነው ባለችው ዒላማ ላይ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ጦርነቱ እሁድ እለት በሁለት ግንባር የተካሄደ ሲሆን፣ በጋዛ ባካሄደችው የአየር ጥቃትም 73 ሰዎች መገደላቸውን የነፍስ አድን ሰራተኞች አስታውቀዋል።
የሂዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ በሆነው ደቡባዊ ቤይሩት ላይ ጥቃቱ የተካሄደው፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በኢራን የሚደገፈው ቡድን መኖሪያ ቤታቸውን ዒላማ በማድረግ ሊገድሏቸው እንደሞከረ ገልጸው ከከሰሱ በኃላ ነው።
የእስራኤል ጥቃት ሃረት ሄሪክ ውስጥ በአንድ መስጊድ እና ሆስፒታል አቅራቢያ የሚገኝ የመኖሪያ ህንፃ መምታቱን የሊባኖስ ብሐራዊ የዜና ማሰራጫ አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በቤይሩት የሚገኘውን "የሂዝቦላህ የስለላ ድርጅት ዋና ማዕከል" እና የምድር ውስጥ ጦር መሳሪያ ማከማቻ መምታቱን እና በሌሎች ጥቃቶች ደግሞ ሦስት የሂዝቦላህ ታጣቂዎች መግደሉን አስታውቋል።
እስራኤል ጥቃቱን ካደረሰች ደቂቃዎች በኃላ፣ ከሊባኖስ አቅጣጫ 70 ሚሳይሎች ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን እና ሁሉንም አየር ላይ እንዳሉ ማክሸፋቸውንም ጦሩ ጨምሮ ገልጿል።
በሌላ በኩል እስራኤል በጋዛ ሰሜናዊ ግዛት ቤይት ላሃ በተሰኘ አካባቢ፣ መኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 73 ፍልስጠማውያን መገደላቸውን የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም