በሰሜን ናይጄሪያ አንድ የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ተገልብጦ በመፈንዳቱ አንድ መቶ የሚሆኑ ሰዎች ሲሞቱ 50 የሚሆኑ ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል።
አብዛኞቹ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡት ከተገለበጠው ቦቴ ላይ ከሚፈሰው ነዳጅ በመውሰድ ላይ ሳሉ ቦቴው በእሳት ተያይዞ በመፈንዳቱ ነው።
የነዳጅ ቦቴው ከሌላ ተሽከርካሪ ጋራ እንዳይጋጭ ለመራቅ ሲሞክር መገልበጡን ፖሊስ አመልክቷል። 94 ሰዎች መሞታቸው መረጋገጡንና እንዲሁም 50 የሚሆኑ መጎዳታቸውን ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል።
ቦቴው መገልበጡን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ከሚፈሰው ነዳጅ ላይ ለመውሰድ ጥረት ሲያደርጉ ፖሊስ ለመከላከል ቢሞክርም ከአቅም በላይ እንደሆነበት ተመልክቷል።
በአስክፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ናይጄሪያ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
በነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች ላይ በተደጋጋሚ አደጋ የሚስተዋል ሲሆን፣ ባለፈው ወር አንድ የነዳጅ አመላላሽ ከሕዝብ ማመላለሻ ጋራ ተጋጭቶ 59 ሰዎች ሞተዋል።
መድረክ / ፎረም