የእስራኤል ታንኮች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ጫፍ ዘልቀው እየገቡ ሲሆን በአካባቢው 9 ቀን ባስቆጠረው የሰሞኑ የእስራኤል ኃይሎች ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ፍልስጤማውያን ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎችም ከዚህ በኋላ የሚሸሹበት ስፍራ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ እስራኤል በሊባኖስ ከምታካሂደው ዘመቻ ጋር በተመሳሳይ ግዜ የሚፈጸም መሆኑን ሮይተርስ በዛሬ እሁድ እኤአ ጥቅምት 13 ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሰሜን ጋዛ ጫፍ ከጋዛ ባህር ዳርቻ የዘለቁት የእስራኤል ወታደሮች በሼክ ረድዋን አንዳንድ ክፍሎች ባደረሱት የቦምብ ጥቃት ነዋሪዎች መኖሪያቸውን እንዲለቁ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፣ የእስራኤል ኃይሎች፣ በሰሜን ጋዛ ጫፍ የሚገኙ ሶስቱን የቤት ሀኖን፣ ጀባሊያ እና የበይት ላህያ ከተሞችን ከተከበበችው ጋዛ በተሳካ ሁኔታ ነጥለዋል፡፡ በጋዛና በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የመገናኛ መስመር በመቁረጥ የተፈቀደላቸውና ፈቃደኛ የሆኑ ነዋሪዎች ብቻ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸውን ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡
የጀባሊያ ነዋሪዎች ቤታቸውን በመልቀቅ ከመሸሽ ሞትን እንደሚመርጡ በማህበራዊ ድረ ገጽ መድረኮች መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሃማስ የሚመራው የጋዛ መንግስት እስራኤል በሰሜን ጋዛ ባደረሰችው ጥቃት 300 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ገልፆ፣ እስራኤል የሰላማዊ ሰዎችን ቤቶች እና መጠለያዎችን ኢላማ አድርጋለች ሲል ከሷል።
ሰሜናዊ ጋዛ 2.3 ሚሊዮን ከሚቆጠር የጋዛ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ይኖርበታል የሚባለው አካባቢ ነው፡፡ እኤአ ጥቅምት 7 ሀማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የአካባቢው ከተሞች በእስራኤል ኃይሎች ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው ቢሆንም ነዋሪዎች እንደገና ወደ አካባቢው መመለስ መጀመራቸው ተነግሯል፡፡
እስራኤል የሀማስ ተዋጊዎች እንደገና እየተሰባሰቡ ነው በማለት ወደ አካባቢው ዘልቃ በመግባት እንደገና ማጥቃት መጀመሯ ተዘግቧል፡፡
የእስራኤል ወታደሮች በሰሜን ጋዛ በርካታ ታጣቂዎች መግደላቸውን እና ፈንጂዎችን እና የጦር መሳሪያዎችን ማግኘታቸውን ሲገልጹ፣ ሃማስ እና ሌሎች አንጃዎች የእስራኤልን ጦር በሮኬት እና በሞርታር ማጥቃት መጀመራቸው በሮይተርስ ዘገባ ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም