የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት በደቡባዊ ሊባኖስ ያሉ 23 መንደር ነዋሪዎች ከአዋሊ ወንዝ በስተሰሜን ወደሚገኙ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ አዘዟል።
ወታደራዊ መግለጫው በአብዛኛው ቀድመውንም ባዶ የነበሩት መንደሮች የእስራኤል ጥቃቶች ዒላማዎች መሆናቸውን ይጠቅሳል።
የእስራኤል ጦር በመንደሮቹ የሄዝቦላ እንቅስቃሴ እየጨመረ በመምጣቱ እና ቡድኑ በዜጎች መካከል የጦር መሳሪያ እየደበቀ በመሆኑ፤ ለነዋሪዎች ደህንነት ሲባል ዜጎች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። ሄዝቦላ የጦር መሳሪያዎቹን በሰላማዊ ሰዎች መካከል መደበቁን አስተባብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እ.ኤ.አ. በ 2006 በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል በተደረገው ጦርነት ወቅት እና አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ካፈናቀለው ጦርነት የላቀ ቁጥር ያላቸው ሊባኖሳዊያን ከመኖሪያ ቀያቸው መሰደዳቸውን ዛሬ ቅዳሜ አስታውቋል።
ጦርነቱን ለማስቆም እየተደረጉ ያሉ አለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እስካሁን ድረስ አልተሳኩም። የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ግን መንግስታቸው የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት “ሙሉ እና አፋጣኝ የተኩስ አቁም” የሚል አዲስ ውሳኔ እንዲያወጣ ይጠይቃል ብለዋል።
የሊባኖስ ጦር አርብ ዕለት እንዳስታወቀው እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ባደረገችው ጥቃት ሁለት ወታደሮቹ መገደላቸውን አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም