በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በተፈናቃይ መጠለያዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች ተባለ


እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት በተገደሉት ፍልስጤማውያን አስከሬን አቅራቢያ ሀዘን የተቀመጡ ቤተሰቦች በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በዴር አል ባላህ በሚገኘው አል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል
እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት በተገደሉት ፍልስጤማውያን አስከሬን አቅራቢያ ሀዘን የተቀመጡ ቤተሰቦች በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በዴር አል ባላህ በሚገኘው አል-አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል

እስራኤል ትላንት ምሽት ባደረሰችው የአየር ጥቃት በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሁለት የተፈናቃይ መጠለያዎች መመታታቸውንና 18 ሲቪሎች መገደላቸውን የፍልስጤማውያኑ የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ጥቃቱ በማዕከላዊ ጋዛ ኑሴራት እና ቡሬጅ የተሰኙ የተፈናቃይ መጠለያዎችን፣ እንዲሁም በሰሜን ጋዛ ደግሞ ጃባሊያ የተሰኘ መጠለያን መምታቱ ታውቋል።

እስራኤል በበኩሏ ዛሬ እንዳስታወቀችው በአየር እና በምድር ጋዛ ውስጥ ያደረሰችው ጥቃት የሐማስ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ ነው።

በተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ፊሊፔ ላዛሪኒ በX ማኅበራዊ መድረክ ላይ እንዳስታወቁት 400ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች በሰሜን ጋዛ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ሆነዋል።

“መሠረታዊ አቅርቦቶች በመሟጠጣቸው፣ ረሃብ እየተስፋፋ መጥቷል” ሲሉም አክለዋል።

በጋዛ የትኛውም ስፍራ ከአደጋ ነፃ አለመሆኑን ስለሚያውቁ፣ ፍልስጤማውያኑ ካሉበት ለቀው እንዲወጡ የሚተላለፈውን ትዕዛዝ መቀበል አቁመዋል ሲሉም አክለዋል ላዛሪኒ።

እስራኤል በተጨማሪም ዛሬ ረቡዕ በደቡብ ሌባኖስ በሄዝቦላ ሚሊሺያዎች ላይ በአየር እና በምድር ጥቃት መፈፀሟ ታውቋል።

ሠራዊታቸው ከሳምንት በፊት የተገደለውን የሄዝቦላ መሪ ሃሳን ናስራላን ሊተካ የታሰብውን ግለሰብ መግደሉን የእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ትላንት ማክሰኞ አስታውቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG