በቱኒዚያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ፣ መራጮች ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል ። ሁነኛ ተችዎቻቸው ወህኒ መወረዳቸውን ተከትሎ ፣ የአሁኑ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ካይስ ሰዒድ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በስልጣን መቆያታቸውን ያረጋግጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
ሰኢድ መጠነ ሰፊ ስልጣን ነጠቃ ከአካሄዱ ከሶስት አመታት በኋላ ምርጫው የቱኒዚያ የዲሞክራሲ ሙከራ የመጨረሻ ምዕራፍ ሆኖ ታይቷል።
ለሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በአምባገነን ስርዓት ላይ የተነሳው የአረብ አብዮት ህዝባዊ አመጽ መፍለቂያ መሆኗ ከአስር አመታት በላይ የኩራት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
የ ሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ 9.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በምርጫው ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል። ከእነዚህ ውስጥ 47 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው በ36 እና 60 መካከል የሚገኙ መሆናቸውንም አክሏል።
ሰኢድ ዛሬ ማለዳ ከቱኒስ በስተሰሜን በምትገኘው በኤንናስር ከተማ በሚገኝ ጣቢያ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ድምጽ ሰጥተዋል።
እ.ኤ.አ. በ2019 በከፍተኛ ድምፅ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ፣ ሰኢድ ህገ መንግስቱን እንደገና ለመጻፍ ያበቃቸው የስልጣን ነጣቃ ፈጽመዋል ።
በተቃዋሚዎች ላይ እየበረታ ያለው የአፈና እርምጃ እና በሁሉም የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎች እስር ቁጥር መጨመሩ ፣ በሀገር ውስጥ እና ውጪ ትችት ቀስቅሷል ።
ዋና መስሪያቤቱን በኒውዮርክ ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዎች “በቱኒዚያ ከ170 በላይ ሰዎች በፖለቲካ ምክንያት ወይም መሰረታዊ መብቶቻቸውን በመጠቀማቸው ታስረዋል” ብሏል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አርብ ዕለት በዋና ከተማዋ ጥብቅ ፖሊስ ቁጥጥር በነበረበት ሀቢብ ቡርጊባ ጎዳና ላይ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል ። ከተቃዋሚዎች መካከል አንዳንዶቹ “ህግን ከአግባብ ውጭ የሚጠቀሙ ፈርዖን” የሚል ምልክት የተጻፈባቸው ሰሌዳዎችን በመያዝ -የ66 አመቱን ሰኢድ አውግዘዋል ።
በእሁዱ ምርጫ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ፣ የቀድሞው ህግ አውጪ እና የሳይድን ወደ ስልጣን መምጣት ሲደግፉ የቆዩት የ59 ዓመቱ ዙሄር ማግዛዊ እና ፣ እጩነታቸው ባለፈው ወር በቦርዱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ እስር ላይ የሚገኙት ብዙም ታዋቂ ያልሆኑት የ47 ዓመቱ አያቺ ዛሜል ናቸው ።
ዛሜል በአሁኑ ጊዜ በምርጫ ለመሳተፍ የተጭበረበረ ፊርማ በማዘጋጀት ክስ ተመስርቶበት ከ14 ዓመታት በላይ እስራት ይጠብቃቸዋል።
የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ ቀዳሚ ውጤቶች ከረቡዕ በፊት መገለጽ እንደሚጀምሩ አስታውቋል ።
መድረክ / ፎረም