ቱርክ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የተፈረመው የመከላከያ እና ምጣኔ ሀብት ስምምነት አካል የሆነ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ሀብት ፍለጋ መርከብ ወደ ሶማሊያ ላከች።
ኡሩች ሪስ በመባል የሚጠራው መርከብ በሶስት ሳምንታት ውስጥ የሶማሊያ የባህር ዳርቻ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።ከዚያም በሶማሊያ የባህር ዳርቻ ላይ (የድምጽ ንዝረትን በመጠቀም ነዳጅን ለማመላከት የሚደረግ) ሴይስሚክ ጥናት ያከናውናል ።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶጋንን ፣ ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት በተገኙበት ቅዳሜ ዕለት በኢስታንቡል የሽኝት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
መርከቧ በሶማሊያ ፍቃድ በተሰጣቸው ሶስት እያንዳንዳቸው 5 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ባላቸው አካባቢዎች ጥናቱን እንደምታከናውን ኤርዶጋን ገልጸዋል።
በመርከቧ የሽኝት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሳተፉት የሶማሊያ ነዳጅ እና ማዕድን ሀብት ሚኒስትር አብዲሪዛክ ሞሐመድ በማዕከላዊ ሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ላይ የሶስት አንጻር (3ዲ) ሴይስሚክ ሙከራ ጥናት እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።ሞሐመድ ሶስቱ ስፍራዎች "ነዳጅ የመገኘት ዕድሉ ጥሩ በሆነበት " የጋሙደግ ባህር ዳርቻ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ አክለዋል ።
ሞሐመድ ለቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት እንደተናገሩት መርከቧ ወደ ምርምር ስፍራዎቹ ከማቅናቷ በፊት ፣የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሚገኙበት የአቀባበል ስነ ስርዓት በሚከናወንባት ሞቃዲሾ ትደርሳለች ።
ጥናቱ መርከቧ ጋላሙደግ ከደረሰችበት ቀን ጀምሮ በ90 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ተገምቷል ።
በሴይስሚክ ምርምር ወቅት መርከቧን የሚያጅቡ ሁለት የቱርክ የባህር ኃይል መርከቦች እንዲሁም አራት ወይም አምስት ሌሎች ድጋፍ ሰጪ መርከቦች እንደሚኖሩ ሞሐመድ ተናግረዋል።
"የሶማሊያን ሀብቶች ለማሰስ ያልቆረጡ ሌሎች ኩባንያዎችም የአሁኑን ፈለግ ይከተላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል ። "የተፈጥሮ ሀብታችንን ለህዝባችን ጥቅም እንጠቀምበታለን፣ መሠረተ ልማታችንን በመገንባት ለሶማሊያ ህዝባች ጥቅም እናውላለን።" ሲሉም አክለዋል።
በመጋቢት ወር ሶማሊያ እና ቱርክ የመከላከያ እና የምጣኔ ሀብት ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አንዱ የሆነውን የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ አሰሳ ውል ገብተዋል።
በነዳጅ ፍለጋ ስምምነቱ መሰረት ፣ ቱርክ የነዳጅ ፍለጋን፣ ምዘናን ፣ነዳጅ ዘይትን ከባህር ዳርቻ ስፍራዎች የማልማት እና የማምረት ስራዎችን እንደምትሰራ የሶማሊያ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም