በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለ ኢራን ጥቃት ምን ይላሉ?


ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳይል በተኮሰችበት ወቅት ፍንጥርጣሪ ነጸብራቅ በሰማይ ላይ ይታይ ነበር።
ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳይል በተኮሰችበት ወቅት ፍንጥርጣሪ ነጸብራቅ በሰማይ ላይ ይታይ ነበር።
በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለ ኢራን ጥቃት ምን ይላሉ?
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:15 0:00

(ዝርዝሩን ከላይ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያገኛሉ)


ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል ጥቃት ልታደርስ እንደምትችል ለእስራኤላውያን የማስጠንቀቂያ የፅሁፍ መልዕክት የደረሳቸው የሚሳይል ጥቃቱ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ነው። በእስራኤል ከ30 አመታት በላይ የኖሩት እና በአውቶቢስ ሹፌርነት የሚተዳደሩት አቶ ተስፋሁን እሸቱ በወቅቱ ስራ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ የማስጠንቀቂያ መልዕክቱ ሲደርስ አሳፍረዋቸው የነበሩት ሰዎች ወርደው ቀድመው ወደተዘጋጁ መጠለያዎች ለመሄድ መበታተናቸውን ይገልጻሉ።

የፅሁፍ መልዕክቱን ተከትሎ በመላ እስራኤል የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደውል ተደወለ። በእየሩሳሌም ከ20 አመት በላይ መኖራቸውን የሚናገሩት እና የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ሊቀመንበር የሆኑት ወይዘሮ ቤተልሔም ካሳ በወቅቱ መኖሪያ ቤታቸው ነበሩ። ደውሉ ሲደወል በሚኖሩበት ህንፃ ያሉ ነዋሪዎች ከህንፃው ስር ወደተዘጋጀው መጠለያ መውረድ ጀምረው ነበር።

ኢራን በሚያዚያ ወር ላይ ተመሳሳይ ጥቃት አድርሳ ነበር። የአሁኑ ጥቃት በመላው እስራኤል ላይ በተመሳሳይ ሰዓት መፈጸሙ ግን በአብዛኛው ሰው ላይ ድንጋጤ መፍጠሩን ነው አቶ ተስፋሁን የሚያስረዱት።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ ማክሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ፣ ጥቃቱን ያካሄደው እስራኤል ቁልፍ በሆኑ የሂዝቦላህ መሪዎች ላይ ለፈፀመችው ግድያ ምላሽ ለመስጠት መሆኑን አስታውቋል። ግማሽ ሰዓት በፈጀው ጥቃትም ከ180 በላይ ሮኬቶችን ተኩሳለች። አቶ ተስፋሁን ይህን ወቅት ከባለቤታቸው ጋር በመኖሪያ ቤታቸው በተዘጋጀ መጠለያ ቢያሳልፉም ሁለት ልጆቻቸው ግን አጠገባቸው አልነበሩም።

እ.አ.አ በ2023 ጥቅምት ወር ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል አንድ አመት ለሚጠጋ ጊዜ በጋዛ ሰርጥ በአየር እና በምድር ጥቃት ስታደርስ ቆይታለች። ያለፉትን ጥቂት ሳምንታት ደግሞ በሊባኖስ በሚገኙ የሂዝቦላ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ እያካሄደች ሲሆን፣ ጦርነቱ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ይስፋፋል የሚለው ስጋት እየተባባሰ ሄዷል። ወይዘሮ ቤተልሔም ይህ ስጋት የነዋሪም መሆኑን ይናገራሉ።

ነዋሪዎቹ ኢራን ለግማሽ ሰዓት ያካሄደችው የሚሳይል ጥቃት ሲያቆም ማምሻውን ጸጥታ መስፈኑን ቢገልጹም ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው ግን ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ነው የሚገፁት።

አቶ ተስፋሁን እንደሚሉት ለአንድ አመት የዘለቀው ጦርነት በእስራኤል ነዋሪዎች ላይ የኢኮኖሚ እና የሥነ ልቦና ጉዳት አድርሷል።

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የሄደው ጦርነት ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚለው ስጋት ዓለም አቀፍ ስጋት ነው። ረቡዕ እለት የእስራኤል ኃይሎች በቤይሩት ደቡባዊ ሰፈሮች ላይ በሚገኙ የሂዝቦላህ ዒላማዎች ላይ አዲስ የአየር ድብደባ ያካሄዱ ሲሆን፣ ታጣቂ ቡድኑ ሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ከሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያ ማካሄዱን ገልጿል።

ጦርነቱ ከፈጠረባቸው ስጋት ተላቀው ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው መመለስ የሚናፍቁት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የእስራኤል ነዋሪዎች ግን በቀጠናው ያለው አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ ተፈትቶ ማየት ይመኛሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG