ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ሠራተኞች እና የኢትዮጵያ መንግስት የአራት-ዓመት 3.4 ቢሊዮን ዶላር የብድር ዝግጅት የመጀመሪያ ግምገማ ለማጠናቀቅ በሚያስችሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን አይ ኤም ኤፍ ትላንት ዓርብ አስታወቀ።
ግምገማው ሲጠናቀቅ "ኢትዮጵያ ወደ 345 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝ ያደርጋታል" ሲልም አይ ኤም ኤፍ ገልጿል።
ስምምነቱ የተቋሙን አስተዳደር እና የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ይሁንታ በሚቀጥሉት ሳምንታት ማግኘት እንዳለበትም አይ ኤም ኤፍ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአይ ኤም ኤፍን ውሳኔ በደስታ መቀበሉን ገልጿል፡፡
እአአ በሃምሌ 29 2024 ከተከፈለው 1 ቢሊዮን ዶላር በተጨማሪ ይህኛውን የመጀመሪያ ግምገማ ማጠቃለያው ተከትሎ ኢትዮጵያ ወደ 345 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ እንደምታገኝን ባንኩ አረጋግጧል፡፡
“የብሄራዊ ባንክ ገዥው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቡድንን ለፍሬያማ ውይይቶች እና ለጠንካራ አጋርነት አመስግኗል" ሲልም ባወጣው ጽሁፍ ላይ ገልጿል፡፡
ሁለቱ አካላት ከስምምነት የደረሱት የአይ ኤም ኤፍ ቡድን ከመስከረም 7 እስከ 16 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በኢኮኖሚ ማሻሽያዎች ትግበራ ባሉ ለውጦች ዙርያ ከኢትዮጵያ ሃላፊዎች ጋር ከመከሩ በኋላ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር መጨረሻ በገበያ ላይ የተመሰረተ የምንዛሪ ተመን፣ ወለድን መሰረት ያደረገ የክትትል ፖሊሲ እና የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጓን አስታውቃለች። ማሻሻያዎቹ ከአይ ኤም ኤፍ እና ከአለም ባንክ ተቀባይነት ማግኘታቸውንም ገልጻለች።
ርምጃው የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ለማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከር፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር፣ የታክስ ገቢን ለመጨመር እና ታዳጊ የልማት ፋይናንሶችን ለመጠቀም ያለመ መሆኑንም ኢትዮጵያ አመልክታለች፡፡ ።
“በሀምሌ ወር መጨረሻ የምንዛሪ ተመን በገበያ ስርዓት እንዲመራ ማድረግን ጨምሮ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ ነው” ሲል አይ ኤም ኤፍ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ በኢትዮጵያ የሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል። "በገበያ ላይ የተመሰረተ ነው" የተባለው የምንዛሪ ተመን ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሸማቾች ከፍተኛ ለሆነ የዋጋ ንረት ተዳርገዋል። ከውሳኔው በፊት 58 ብር የነበረው የዶላር ምንዛሬ በአሁኑ ወቅት ከ112 ዶላር በላይ እየተመነዘረ ይገኛል፡፡
ከሸማቹ ስጋት አንፃር የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን አሉታዊ ውጤቶች ለመቆጣጠር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጿል።
መድረክ / ፎረም