ዩክሬን በሰው አልባ አውሮፕላኖች በሩስያና ክሪምያ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ፍንዳታ መከሰቱንና አውራ ጎዳናዎች መዘጋታቸውን የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እና የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቀዋል፡፡
ትላንት ሌሊት ከመቶ በላይ በሚሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ዩክሬን አድርሰዋለች የተባለው ይህ ጥቃት የተፈጸመበት ቦታ ባለፈው ረቡዕ በተመሳሳይ ጥቃት ተመቶ አስራ ሶስት ሰዎች ተገድለዋል ከተባለው ሌላው የጦር መሳርያ ማከማቻ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡
ፍንዳታውን ተከትሎ ዛሬ የሩሲያ ባለስልጣናት 100 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የባቡር መንገድ ዘግተው ተሳፋሪዎችን በአቅራቢያው ከሚገኝ የባቡር ጣቢያ እንዲወጡ አድርገዋል፡፡
በሌላ በኩል በደቡባዊ ምዕራብ ሩሲያ የሚገኝ የጥይት መጋዘን እና የሚሳኤል የጦር መሣሪያ ማከማቻ ላይ ዛሬ በደረሰ ሌላ ጥቃትም የእሳት ቃጠሎውን ተከትሎ ፍንዳታዎች በመከሰታቸው ነዋሪዎች አካባቢው እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በማህበራዊ ሚድያ በወጡ የቪድዮ ምስሎች በአካባቢው ያለማቋረጥ ፍንዳታዎች ሲሰሙና ብሩህ ብርቱካናማ ደመና ወደ ሰማይ ሲወጣ ታይቷል፡፡
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ማለዳ ላይ ጦሩ በክሪምያና በሩስያ ግዛቶች በአንድ ሌሊት 101 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተኩሶ መጣሉን አስታውቋል፡፡በሁሉም የሩስያ ክልል በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡
መድረክ / ፎረም