በኒውዮርክ ከተማ እስላማዊ መንግስትን በመደገፍ የጅምላ ጥቃት ለማካሄድ አቅዷል በሚል የ20 ዓመቱ ፓኪስታናዊ መሀመድ ሻህዜብ ካን ተከሰሰ፡፡
ጥፋተኝነቱ ከተረጋገጠ "እስከ 20 አመት የሚደርስ እስራት ይጠብቀዋል" ሲል የዩናትይድስ ፍትህ ሚኒስቴር ትላንት ዐርብ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ካን የተከሰሰው በእስራኤል የሐማስ ጥቃት የተካሄደበት አንደኛ ዓመት በሚታሰብበት እኤአ ጥቅምት 7 ቀን፣ በኒውዮርክ ብሩክሊን በሚገኘው የአይሁድ ማእከል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አሲሯል በሚል ነው።
የካናዳ ፖሊስ ተከሳሹን በቁጥጥር ስር ያዋለው ባለፈው ረቡዕ እኤኤ መስከረም 4 በአሜሪካ እና ካናዳ ድንበር አቅራቢያ በኦርምስታወን ኩቤክ ሞንትሪያል ከተማ ውስጥ ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ካን እኤአ ከህዳር 2022 ጀምሮ የእስላማዊ መንግሥትን ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨትና በማህበራዊ ሚዲያ ለቡድኑ ድጋፉን ሲገልጽ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ካን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ የአይሁድ ማህበረሰብ ማዕከላትን ኢላማ ያደረገ ከእይታ ውጭ የሆነ ድብቅ የእስላማዊ መንግሥት የጥቃት ሰንዛሪ ቡድን ለማቋቋም በሚስጥር ይወያይ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ለዚህም ተግባር የሚውሉ ልዩ ልዩ የስለት፣ ተተኳሽና ፈንጂዎችን የመሳሰሉ የጥቃት መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጉ በውይይቶቹ ማመልከቱም ተጠቅሷል፡፡
መድረክ / ፎረም