የእስራኤል መንግስት ከሐማስ ጋራ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ግፊት ለማድረግ በሚል ትልቁ የሠራተኛ ማኅበር በጠራው የሥራ ማቆም አድማ ባንኮች፣ የሕዝብ መጓጓዣዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የንግድ ሱቆችና ዋናው የአየር ማረፊያ አገልግሎታቸው ተስተጓጉሎ ውሏል።
አድማው የተጠራው በሐማስ እጅ የነበሩ ስድስት ታጋቾች ተገድለው መገኘታቸውን ተከትሎ ነው።
የሠራተኛ ማኅበሩ ሊቀ መንበር አረን ባር-ዴቪድ በጋዛ በሐማስ የታገቱትን ማስለቀቅ “እጅግ አንገብጋቢው ጉዳይ ነው” ብለዋል።
“ከዳር ቆመን መመልከት አንችልም፣ በጋዛ የምድር መተላለፊያ ውስጥ በመሞት ላይ ያሉ ልጆቻችንን ጩኸት ችላ ማለት አንችልም” ሲሉም ተደምጠዋል የሠራተኛ ማኅበሩ ሊቀ መንበር።
ስድስቱ ታጋቾች የተገደሉት የእስራኤል ኃይሎች እየተቃረቡ መምጣታቸውን በተመለከቱ የሐማስ ታጣቂዎች መሆኑንና በቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት መሆኑንም የምርመራ ውጤት ማመልከቱን የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ አስታውቋል።
የዛሬው የሥራ ማቆም አድማ የተደረገው፣ ትላንት እሁድ በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች የእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በመጠየቅ ሰልፍ ማደረጋቸውን ተከትሎ ነው።
መድረክ / ፎረም