የእስራኤል ጦር በፍልስጤም ግዛት ዌስት ባንክ ሶስተኛውን ቀን ባስቆጠረው ጥቃት ጄኒን ከተማ ላይ የአየር ድብደባ ፈፅሟል ሲሉ ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡
የእስራኤል ጦር ካላፈው ማክሰኞ ጀምሮ 19 ሰዎች የተገደሉባቸው ጥቃቶች “የሽብረተኞች ምሽግ” ላይ ያነጣጠሩ” እና በሰሜናዊ ዌስት ባንክ የተካሄዱ ጥቃቶችን ለመከላከል ያለሙ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
እንዲህ ያሉት ጥቃቶች ወራትን ባስቆጠረው የእስራኤልና ሀማስ ግጭት የተለመዱ ቢሆንም በዌስት ባንክ ብዙ ጊዜ የሚታዩ አለመሆናቸውን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ፍልስጤማውያን ጥቃቶቹ የጋዛ ግጭትን እንደ ማራዘሚያ ለመጠቀምና የእስራኤልን ወታደራዊ ቁጥጥር ለማስቀጠል የሚደረግ ሙከራ አድርገው ነው እንደሚመለከቱትም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በጋዛ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ኢሚሬትስ ሆስፒታል ሲያደርስ የነበረን የተሽክርካሪ አጀብ (ኮንቮይ) በሚሳዬል በመምታቷ የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል።
እስራኤል በተሽከርካሪዎቹ ውስጥ ታጣቂዎች እንደነበሩ ብትናገርም ከገለልተኛ ወገን አለማረጋገጡን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
የእስራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ በካን ዮኒስ እና በዲር አል ባላህ አካባቢዎች አጠናቅቄያለሁ ባለው ትልቅ ወታደራዊ ዘመቻ 250 ታጣቂዎችን ገድሎ የ6 ታጋቾችን አስከሬን ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ሃማስ ወደ እስራኤል ግዛት ዘልቆ በመግባት ጥቃት ከፈጸመበት እኤአ ጥቅምት 7 ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ግጭት ከ40,000 በላይ ፍልስጤማውያንን ለሞት መዳረጉን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ይገልጻሉ።
መድረክ / ፎረም