ለሦስት ቀናት ጉብኝት፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. መቐለ የገቡት በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ እና ከህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋራ በተናጠል ተወያይተዋል።
ውይይቱን ፍሪያማ ሲል የገለፀው በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ፣ በትግራይና በአካባቢው ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ያለውን መሠረታዊ አስፈላጊነት በትኩረት መናገራቸውን አመልክቷል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳም፣ ከአምባሳደር ማሲንጋ ጋራ “ለትግራይ በጣም አስፈላጊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል፤” ሲሉ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ጉዳይ እና የፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸም፣ በውይይቱ ከተነሡት ጉዳዮች መካከል መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉም ይኹን በአገር አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቀስቃሴ ስለሚያስፈልገው ድጋፍ መነጋገራቸውንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል፣ አምባሳደር ማሲንጋ፣ ለሁለት ከተፈለው የህወሓት አመራር የአንዱ ቡድን ሊቀ መንበር ከኾኑት ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋራ መወያየታቸውን፣ ለውይይቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮችም ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀዋል ።።
አምባሳደር ማሲንጋ በመቐለ የተገኙት፣ ለሁለት የተከፈሉት የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች ልዩነት እየጎላ መምጣቱ በታየበት ወቅት ነው።
በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት፣ ዛሬ ያካሔዷቸው የተናጠል ውይይቶች አንዱ አጀንዳ ስለመኾኑ ግን፣ ኤምባሲውም ሆነ የክልሉ አመራሮች እስከ አሁን በይፋ የገለጹት ነገር አለመኖሩን፣ መቐለ የሚገኘው ሪፖርተራችን ሙሉጌታ ኣጽብሐ ዘግቧል።
መድረክ / ፎረም