የዩክሬን ጦር አዛዥ በዛሬው ዕለት በሰጡት አስተያየት የኪየቭ ኃይሎች ባለፉት ሶስት ሳምንታት ባካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻ 1,300 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የሩሲያ ኩርስክ ግዛት መቆጣጠራቸውን እና በሩስያ ኅያሎች ተይዘው የሚገኙ ዩክሬይናውያንን ለማስለቀቂያ ያሰቧቸውን 594 ሩስያውያን መማረካቸውን ተናግረዋል።
ጄኔራል ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ሲናገሩ፤ በዩክሬን ጦር ግስጋሴ የተነሳ “የጥቃት እርምጃ እየፈጸመ ባለው ኃይላችን ዙሪያ የመከላከያ ቀለበት ለማበጀት እና የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ለማቀድ” በታለመ ጥረት ሩስያ ኃይሎቿን ከሌሎች አካባቢዎች እያጓጓዘች ነው ብለዋል።
ከ2ተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ወደ የሩስያን ምድር ዘልቆ በመግባት በግዝፈቱ የመጀመሪያው መሆኑ የተነገረለት በከርስክ የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ 130, 000 ያህል ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስገደዱ ተዘግቧል። የዩክሬይን ኃይሎች ጥቃት ለመመከት ሩስያ አጋዥ ኃይል ወደ አካባቢው መላኳ ቢገለጽም፤ እርምጃው የሩስያ ኃይሎች በስፋት በተቆጣጠሯቸው የምሥራቃዊ ዩክሬን አካባቢዎች ያላቸውን ይዞታ የቱን ያህል ሊያዳክም እንደሚችል በውል አልተለየም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘለንስኪ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት “ሩስያ የጦርነቱ ማዕከል ከሆነውና በዝግታ እየዘለቀች ከነበረችበት ከምሥራቃዊ ዩክሬኗ ዶኔስክ ወታደሮቿን ወደ ከርስክ እያዛወረች አይደለም” ብለዋል። ይሁን እንጂ ኃይሎቻቸው በከርስክ እያካሄዱ ያሉት ወታደራዊ ዘመቻ የሩስያን ከከርስክ በስተምዕራብ በሚገኙት የሰሚ እና በካርኪቭ ግዛቶች ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን የመቆጣጠር ኢላማ አምክኗል” ሲሉ ዘለንስኪ አክለዋል።
መድረክ / ፎረም