በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ አሁንም የኢትዮጵያ ወታደሮች በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ እንዲሳተፉ አትፈቅድም


የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ

የሶማሊያ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ከተፈራረመችው አወዛጋቢ የመግባቢያ ስምምነት እስካልወጣች ድረስ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከመጪው የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ በአጭር አጠራሩ አውሶም (AUSSOM) አካል እንዲሆኑ እንደማይፈቅዱ በድጋሚ አስጠነቀቁ፡፡

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነቱን ካላቋረጠች ኃይሎችዋ የመጭው የአውሶም ተልእኮ አባል እንደማይሆኑ በዚህ ሳምንት ምቃድሾ ውስጥ ተናግረዋል፡፡

አውሶም ከአሁኑ የአፍሪካ ህብረት እኤአ ጥር 2025 ተልእኮውን የሚቀበል ሲሆን በሶማልያ ለሶስት ዓመታት ተሰማርቶ ይቆያል፡፡

በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የቀሰቀሰው የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ነፃነት ዕውቅና እንድትሰጥና በለውጡ 20 ኪሎ ሜትር የቀይ ባህር ጠረፍ እንድታገኝ የሚያስችል መሆኑን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ሶማሊያ ይህን የመግባባቢያ ስምምነቱን የምትመለከተው ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነትዋን እንደ ሚጥስ አድርጋ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ ለአውሶም የመጨረሻው የፖለቲካ፣ የፋይናንስ እና የሎጂስቲክስ ዝግጅቶች በዓመቱ መጨረሻ እንደሚጠናቀቁ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአውሶም ተልዕኮ ትሳተፍ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ተድላ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ከገመገመች እና ከአጋሮቿ ጋር ከመከረች በኋላ ትወስናለች” ብለዋል።

" ሁኔታውን እና እየተካሄደ ያለውን በቅርበት እየተከታተልን ነው። በሶማሊያ የጸጥታ ስጋት አለን። በምናደርገው ግምገማ እና ሶማልያ ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ ካሉ ከአካባቢው አጋሮቻችን ጋር በመስራት ወደፊት የምናደርጋቸውን ነገሮች እንወስናለን” ሲሉም አቶ ተደላ አክለዋል፡፡

ሶማልያ የማትቀበለው ቢሆንም የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር በአውሶም ተልዕኮ ይሳተፍ እንደሆን የተጠየቀቱ አቶ ተድላ

“ይህ የሃሰን ሼክ መሃሙድ እና የጥቂት ቅርብ ባልደረቦቻቸው ወይስ የፌደራሉ ክልሎች ውስጥ ያሉ ሶማልያ ፖለቲካ ልሂቃን በሙሉ አቋም ነው? የዚህን መልስ ለአንተ ተዋለሁ?”በማለት መልሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሶማልያ ውስጥ የተሰማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አሉዋት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከፊሎቹ በአፍሪካ ህብረት ተልእኮ ውስጥ የተሰማሩ ሲሆኑ ሌሎቹ በሁለት አገሮች የጋራ ስምምነት መሰረት የተሰማሩ ናቸው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG