በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤምፖክስ ምን አይነት በሽታ ነው? እንዴትስ በቁጥጥር ስር ማዋል ይቻላል?


ሰሜን ጎማ ውስጥ በሚገኝ የኤምፖክስ ህክምና ማዕከል ውስጥ አንዲት ህፃን በእናቷ እየታገዘች ህክምና ሲደረግላት - ነሐሴ 17, 2024
ሰሜን ጎማ ውስጥ በሚገኝ የኤምፖክስ ህክምና ማዕከል ውስጥ አንዲት ህፃን በእናቷ እየታገዘች ህክምና ሲደረግላት - ነሐሴ 17, 2024

ስዊድን በመካከለኛው እና በምስራቅ አፍሪካ ዙሪያ እየተሰራጨ ያለውን፣ በቀድሞ አጠራሩ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) ተላላፊ በሽታ በሀገሯ ማግኘቷን ሐሙስ እለት አስታውቃለች። ይህ የኤምፖክስ አደገኛ የተባለው ዝርያ ከአፍሪካ ውጭ ሲታይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ ስዊድን በሽታው መገኘቱን ያስታወቀችው የዓለም ጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኤምፖክስ ወረርሽኝ ወደ ሌሎች 12 ሀገራት መዛመቱን ተከትሎ ጉዳዩ አስቸኳይ የማኅበረሰብ ጤና ስጋት መሆኑን ካወጀ ከአንድ ቀን በኃላ ነው።

ለመሆኑ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተብሎ ይጠራ የነበረው ኤምፖክስ ምን አይነት በሽታ ነው? በየትኛው የዓለም ክፍል ነው የተስፋፋው?

በቀድሞ አጠራሩ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመባል ይታወቅ የነበረው የኤምፖክስ በሽታ በአፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ በመምጣቱ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ተሻግሮ ሊስፋፋ ይችላል ሲል ረቡዕ እለት ጉዳዩ የማኅበረሰብ ጤና ስጋት መሆኑን አውጇል። የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል በበኩሉ በሽታው በአህጉሩ ላይ የማህበረሰብ ጤና ስጋት መሆኑን ይፋ ያደረገው ማክሰኞ እለት ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ ውሳኔውን ያሳወቁት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጤና ተቋም አስቸኳይ ስብሰባ ከአካሄደ በኃላ ሲሆን፣ እንደተሰጋው የስዊድን ባለሥልጣናት አደገኛ የተባለው የኤምፖክስ ዝርያ ቫይረስ ያለበት ሰው ማግኘታቸውን ሐሙስ እለት ይፋ አድርገዋል።

የጤና ድርጅቱ እንዳለው በዚህ አመት ብቻ በአፍሪካ ከ14 ሺህ በላይ ዜጎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን 524 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ የጨመረ መሆኑንም አመልክቷል።

እስካሁን ከተመዘገበው የሞት ቁጥር ከ96 በመቶ በላይ የሚሆነው በኮንጎ ውስጥ ቢሆንም፣ ሳይንቲስቶች አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ በቀላሉ በሰዎች መካከል ሊተላለፍ ይችላል በሚል ስጋት ገብቷቸዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ቢሮ ተጠባባቂ ድንገተኛ ክስተቶች ስራ አስኪያጅ ሳም ቦላንድ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር በአደረጉት ቆይታ እንዳስረዱት፣ በሽታው ከየት እንደመጣ እና የመጀመሪያው ታማሚ ማን እንደነበር በግልፅ አይታውቅም።

ኤምፖክስ በሽታ ምን አይነት በሽታ ነው? እንዴትስ በቁጥጥር ስር ማዋል ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አሶስዬትድ ፕሬስ በበሽታው ዙሪያ ባወጣው ማብራሪያ፣ በሽታው ለመጀመሪያ የታወቀው ጊዜ እ.አ.አ በ1958 ሳይቲስቶች በዝንጀሮዎች ሰውነት ላይ ጠባሳ የሚተው ወረርሽኝ ባስተዋሉ ጊዜ መሆኑን አመልክቷል።


እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በበሽታው የተያዙት ሰዎች በመካከለኛው እና በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ንክኪ የነበራቸው ሰዎች እንደነበሩም ገልጿል።

እ.አ.አ በ2022 ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ በጾታዊ ግንኙነት እንደሚሰራጭ የተረጋገጠ ሲሆን ከዚህ በፊት የኤምፖክስ በሽታ መኖሩ ባልታወቀባቸው ከ70 በላይ ሀገሮች ውስጥ ወረርሽኙ መከሰቱን አሶስዬትድ ፕሬስ አመልክቷል።

ኤምፖክስ እንደ ፈንጣጣ ከመሳሰሉ ቫይረሶች ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን እንደ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት እና የሰውነት ሕመም የመሳሰሉ ምልክቶች አሉት። በሽታው የተባባሰባቸው ሰዎች ደግሞ በፊታቸው፣ እጆቻቸው፣ ደረታቸው እና የመራቢያ አካላቸው ላይ ቁስለት ሊኖራቸው ይችላቸው።

በአፍሪካ ለምን ከፍተኛ ስጋት ፈጠረ?

ሰሜን ጎማ ውስጥ በሚገኝ የኤምፖክስ ህክምና ማዕከል ውስጥ ህሙማን የምክር አገልግሎት ሲሰጣቸው - ነሐሴ 17, 2024
ሰሜን ጎማ ውስጥ በሚገኝ የኤምፖክስ ህክምና ማዕከል ውስጥ ህሙማን የምክር አገልግሎት ሲሰጣቸው - ነሐሴ 17, 2024

በአፍሪካ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ድንገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል በሽታው ቢያንስ በ13 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ መገኘቱን አስታውቋል። ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸርም በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ160 ከመቶ፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ በ19 ከመቶ ጨምሯል። የዓለም ጤና ድርጅት የማኅበረሰብ ጤና ስጋት መፍጠሩን ይፋ ያደረገውም በዚህ ምክንያት ነው።

በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ፣ ኮንጎ ውስጥ በሚገኝ የማዕድን ማውጫ ከተማ ውስጥ፣ በቀላሉ ሊሰራጭ እና እስከ 10 ከመቶ የሚደርሱ ሰዎችን ሊገድል የሚችል አዲስ ኤምፖክስ ቫይረስ ዝርያ መገኘቱን ሳይንቲስቶች ይፋ አድርገው ነበር።

ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት በተከሰቱት የኤምፖክስ ወረርሽኞች፣ ቁስሎች በብዛት በደረት፣ እጆች እና እግሮች ላይ ይታዩ የነበሩ ሲሆን፣ አዲሱ የቫረሱ ዝሩያ ግን በመራቢያ አካላት ላይም ቀለል ያሉ ምልክቶች እና ቁስሎችን እንደሚያስከትል አሶስዬትድ ፕሬስ አመልክቷል። ይህም በቀላሉ በሽታውን ለመለየት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ሳያውቁ ለሌሎች ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ዘገባው የኮንጎ ተመራማሪ የሆኑንትን ዶክተር ፕላሲዴ እምባላ ኢንጌቤኒን ጠቅሶ አብራርቷል።

በዋናነት በማዕከላዊ እና በምዕራብ አፍሪካ ይገኝ የነበረው ኤምፖክስ በቅርቡ በአራት የምስራቅ አፍሪካ አገራት - ማለትም በብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ መገኘቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ሁሉም ወረርሽኞች ኮንጎ ካለው ወረርሽኝ ጋር የተገናኙ ሲሆን የጤና ድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር፣ በሽታው በአፍሪካ ውስጥ እና ከአህጉሩ ውጪም ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን አስታውቀው ነበር።

በአይቮሪ ኮስት እና በደቡብ አፍሪካም፣ እ.አ.አ በ200 በዓለም ዙሪያ የተሰራጨው እና ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ያጠቃው ብዙም አደገኛ ያልሆነ የኤምፖክስ ቫይረስ ዝርያ መከሰቱን አስታውቀዋል።

ለተቀረው ዓለም የደቀነው ስጋት ምን ይመስላል?

ልክ እንደማንኛውም ተላላፊ በሽታ፣ በኮንጎ የተከሰተው አዲሱ ኤምፖክስ ቫይረስ በአራት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተገኝቷል። ከአፍሪካ ውጪም ለመጀመሪያ ጊዜ በስዊድን የኤምፖክስ ቫይረስ ያለበት ሰው መገኘቱን የሀገሪቱ የሕዝብ ጤና ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል።

ኤምፖክስ
ኤምፖክስ

የስዊድን ባለስልጣናት በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ህዝቡ ላይ የተጋረጠው አደጋ "በጣም ዝቅተኛ" ተደርጎ የሚቆጠር ነው ቢሉም አልፎ አልፎ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከውጪ ሊገቡ እንደሚችሉ ግን አመልክተዋል። ሆኖም አሶስዬትድ ፕሬስ እንደሚለው፣ እንደ ኮቪድ 19 እና ኩፍኝ ከመሳሰሉ በሽታዎች ጋር ሲነፃፀር፣ ኤምፖክስ አየር ወለድ በሽታ ባለመሆኑ ከሰው ወደ ሰው ለመተላለፍ የቆዳን ንክኪ የሚጠይቅ ነው። ዘገባው አክሎም፣ የበለጸጉ ሀገራት ኤምፖክስን ለማስቆም ካላቸው ሀብት ጋር ሲነፃፀር፣ ቫይረሱ ቢገኝ እንኳን ስርጭቱን በፍጥነት ማስቆም እንደሚችሉ አመልክቷል።

ኤምፖክስን እንዴት ማስቆም ይቻላል?

እ.አ.አ በ2022 በበርካታ ሀገሮች የተከሰተውን የኤምፖክስ ወረርሽኝ፣ ሰዎች ተጋላጭ ከሚያደርጓቸው ባህሪያት እንዲታቀቡ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በበለጸጉ ሀገራት ክትባቶችን እና ሕክምናዎችን በመጠቅም ማስቆም ተችሏል። ነገር ግን አሶስዬትድ ፕሬስ ክትባቱም ሆነ ሕክምናው እስካሁን በአፍሪካ እንደማይገኝ ያመለክታል።

ፋይል - ይህ እ.አ.አ ነሐሴ 10፣ 2022 የተነሳው ፎቶ፣ በሰሜን ፈረንሳይ ውስጥ የኤምፖክስ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ሲሰጥ ያሳያል።
ፋይል - ይህ እ.አ.አ ነሐሴ 10፣ 2022 የተነሳው ፎቶ፣ በሰሜን ፈረንሳይ ውስጥ የኤምፖክስ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ሲሰጥ ያሳያል።

በለንደን የሃይጂን እና ትሮፒካል ሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑትን ተመራማሪ ጠቅሶ ያብራራው አሶሽዬትድ ፕሬስ፣ እንደ ፈንጣጣ የመሳሰሉ ተዛማጅ ቫይረሶችን ጨምሮ ክትባቶች መጠቀም በሽታውን ለመቆጣጠር ያስችላል።

የኮንጐ ባለስልጣናት 4 ሚሊየን የክትባት ጠብታ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን የኮንጎ ኤምፖክስ ምላሽ ኮሚቴ አስተባባሪን ጠቅሶ የዘገበው አሶስዬትድ ፕሬስ፣ እስካሁን ግን ምንም ክትባት እንዳላገኙም አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG