በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአቶ ጌታቸው ቡድን የተጠራ "ህወሓትን የማዳን" ስብሰባ በመቐለ ተካሔደ 


የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ
የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ

ለሁለት ከተከፈለው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) አመራር አንዱን ቡድን በሚመሩት የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተጠራ “ህወሓትን የማዳን” የተባለ ስብሰባ፣ ዛሬ እሑድ፣ በመቐለ ከተማ ተካሒዷል።

የአቶ ጌታቸው ቡድን፣ ዛሬ እሑድ፣ ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ስብሰባውን ያደረገው፣ በፓርቲው ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ቡድን፣ ባለፈው ማክሰኞ የጀመረውን ጉባኤ እያካሔደ ከሚገኝበት የሰማዕታት ሓውልት አዳራሽ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል በማይርቀው በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ ነው።

በዚኽ ስብሰባ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት፣ እንዲሁም ከመቐለ ከተማ፣ ከዞንና ከወረዳዎች የተወከሉ የፓርቲው አመራሮች መሳተፋቸውን፣ የመቐለ ዘጋቢያችን ሙሉጌታ ኣጽብሓ ከቦታው ዘግቧል።

የሰብሰባው ተሳታፊዎች
የሰብሰባው ተሳታፊዎች

አቶ ጌታቸው ባሰሙት ንግግር፣ ስብሰባው፥ "ተቋማዊ ነጻነታቸውን ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች፣ ፓርቲያቸውን ለማዳን የሚሳተፉበት ውይይት ነው፤" ብለዋል።

በዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራውና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያልሰጠውን ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሔደ የሚገኘው ሌላው ቡድን፣ ትላንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፣ በ13ኛው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሥራ ዘመናቸው መጠናቀቁን ጠቅሶ፣ ከእነርሱ መካከል የኾኑትንና በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አድርጎላቸው ያልተገኙትን 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላት፣ በፓርቲው ስም እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱ ይታወሳል። 14ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ከተሠየመበት ዕለት አንሥቶ፣ "እንደ ተራ አባል" እንጂ እንደ አመራር ፓርቲውን መወከል እንደማይችሉም አስታውቋል።

ባለፈው ማክሰኞ የተጀመረው የዚኽኛው ቡድን ጉባኤ፣ ዛሬ እሑድ ለስድስተኛ ቀን ቀጥሎ መዋሉንም፣ ሙሉጌታ አጽብሓ ከስፍራው ዘግቧል።

የጉባኤው ዝግጅት ሒደት፣ "የህወሓትን መተዳደሪያ ደንብ እና የአገሪቱን ሕግ የጣሰ ነው" ያለው የአቶ ጌታቸው ቡድን "ሕገ ወጥ ነው" በሚል መኮነኑ ይታወሳል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG