በአሜሪካ ኮሎራዶ በተካሄደው የአየር ላይ ትርዒት ተመልካቾች መካከል በአካባቢው በነበረው ከባድ ሙቀት ምክንያት አንድ መቶ የሚሆኑት አስቸኳይ ህክምና ሲፈልጉ አስር የሚሆኑት ደግሞ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡
ትላንት ቅዳሜ በተጀመረውና ዛሬም በሚቀጥለው “ ፓይክስ ፒክ ሪጅናል ኤር ሾው” በመባል የሚታወቀው ይህ ትርዒት በታዋቂው የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል “ ሰማያዊ መላእክት” በሚል ስም የሚታወቁት የበረራ ኤግዚቢሽን ቡድን ትርኢት የሚያሳዩበት እና የተለያዩ አይነት ዘመናዊ እና አንጋፋ አውሮፕላኖችን የሚታዩበት ነው፡፡
የኮሎራዶ ስፕሪንግስ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፈው መግለጫ አብዛኛዎቹ ታካሚዎች በድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች ህክምና እንደተሰጣቸው አስታውቋል፡፡
የእሳት አደጋ መከላከያው ሃላፊ ራንዲ ሮያል አዘጋጆቹ ና የድንገተኛ አደጋ ሃላፊዎች ወስደውታል ባሉት ፈጣን ምላሽ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በፑብሎ፣ ኮሎራዶ የሚገኘው ብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት፣ ቅዳሜ ከሰአት በኋላ በአካባቢው እስከ 37.7 ሴልሺየስ የሚደርስ የሙቀት መጠን እንደሚጠበቅ በማስታወቅ የማስጠንቀቂያ ምክር ሰጥቶ እንደነበረም ተገልጿል፡፡
መድረክ / ፎረም