የጋዛ ሲቪል መከላከል ተቋም ዛሬ ቅዳሜ ጧት በተካሄደው የእስራኤል አየር ጥቃት ዘጠኝ ህጻናትና ሶስት ሴቶችን ጨምሮ 18 የአንድ ፍልስጤማውያን ቤተሰብ አባላት ተገድለዋል ብሏል፡፡
የአየር ጥቃቱ በማዕከላዊ ጋዛ አል-ዛዋይዳ ሰፈር የሚገኘውን የአጃላህ ቤተሰብ ቤት መምታቱን የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል ለኤኤፍፒ ተናግረዋል። የእስራኤል ጦር ስለጉዳዩ አስተያየት አልሰጠም።
“በአጅላህ ቤተሰብ እና በአል-ዛዋይዳ መጋዘን ላይ በደረሰው የእስራኤል ጥቃት 18 ሰዎች ሙተዋል።" ያሉት ባሳል ዘጠኝ ህጻናት እና ሶስት ሴቶችን ጨምሮ የሟቾችን ስም ዝርዝር ገልጸዋል፡፡
የዐይን ምስክሮች ጥቃቱ ከእኩለ ሌሊት በኋላ እንደተፈጸመ ተናግረዋል፡፡
"ሶስት ሮኬቶች ቤቱን በቀጥታ ነው የመቱት" ሲሉ አህመድ አቡ አል ጉውል የነፍስ አድን ሰራተኞች ከተደመሰሰው መኖሪያ ቤት ፍርስራሽ ውስጥ አስከሬኖች ሲያወጡ ተናግረዋል።
የዛሬው ግድያ የተሰማው 10 ወራት በዘለቀው ጦርነት የሞቱት ሰዎች ከ40ሺ መድረሱን ሀማስ በተነገረበት ሰሞን ነው፡፡
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ከ10 ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት ሰፊ የጋዛ አካባቢዎችን አወድሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ የተኩስ አቁም ለማምጣት ካታር ዶሃ ላይ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሁለት ቀናት ንግግር ትናንት ዓርብ መጠቃለሉንና በመጪው ሳምንት ካይሮ ላይ ከስምምነት ለመድረስ መታቀዱን አደራዳሪዎቹ አስታውቀዋል።
ምንም እንኳ ሃማስ በንግግሩ ባይሳተፍም አደራዳሪዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ግብጽ እና ካታር በትላንቱ መግለጫቸው ንግግሩ ገንቢ እንደነበርና በጥሩ መንፈስ የተደረገ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መድረክ / ፎረም