በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማልያ 10 ታጣቂዎችን በሞት ቀጣች


የአል ሸባብ ተዋጊዎች
የአል ሸባብ ተዋጊዎች

ሶማልያ ውስጥ ግድያና ጥቃት ፈጽመዋል በሚል የተከሰሱ አስር የአልሸባብ ታጣቂዎች በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልኬዮ ከተማ ዛሬ ቅዳሜ በሞት መቀጣታቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡

በክልሉ ፖሊስ አዛዥ ኮሎኔል አብዲሃኪም መሀሙድ ዩሱፍ የተነበበው መግለጫ አስሩ ታጣቂዎች ቀደም ሲል በሙዱግ ክልል ከተፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያዎች በስተጀርባ እጃቸው አለበት ብሏል፡፡

የሶማሊያ ፑንትላንድ ክልል ባሥልጣናት በሌሉበት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውና በጥቃቱ የተሳተፉ ሶስት የቡድኑ አባላትም እየታደኑ ናቸው ብለዋል፡፡

የሶማልያ ፖሊስ ኃላፊዎች በሽሽት ላይ የሚገኙት የቡድኑ አባላት በተገኙበት ቦታ እንዲገደሉ ለጸጥታ ኃይላት ትዕዛዝ መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡

ፑንትላንድ በአልሸባብ ቡድን አባላት ላይ ትልቁን የሞት ቅጣት የፈጸመችው እኤአ 2021 በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ ነበር፡፡

በወቅቱ የጋልካዮ ባለሥልጣናት 18 የአልሸባብ ታጣቂዎች ላይ የሞት እምርጃውን ተግባራዊ ያደረጉት የዛሬው ቅዳሜ ርምጃ በተወሰደበት ተመሳሳይ ስፍራ መሆኑም ተነግሯል፡፡

18ቱ ታጣቂዎች የተፈረደባቸው የጸጥታ ሠራተኞች እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ የእውቅ የማህበረሰብ መሪዎች ላይ ለዓመታት በፈጸሙት ግድያ ነው፡፡

ሶማልያ ውስጥ ባሉ ታጣቂዎች ላይ የሚመሰረቱ ክሶች የሚታዩት በወታደራዊ ችሎቶች ነው፡፡

መሰረቱን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተመልካች ድርጅት ቀደም ሲል ባወጣው ሪፖርት፣ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶቹ “ ዓለም አቀፉን የፍትህ አሰጣጥ ሂደት ደረጃ የጠበቁ አይደሉም” ሲል የሲቪሎች ጉዳዮች በመደበኛው ፍርድ ቤቶች እንዲያታዩ አሳስቧል፡፡

አብዛኞቹ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ባለሥልጣናት ግን አልሸባብ የሶማልያ መንግሥትን ለመገልበጥ ሰው ጨራሽ በሆነ ጦርነት የተሰማራ ታጣቂ ቡድን ስለሆነ እንደ ወታደር ይዳኛል ሲሉ ችሎቶቹን ተከላክለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG