በሰሜን ጋዛ ወደ መጠለያ በተቀየረ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት ፣በአካባቢው የጤና ባለስልጣናት አሃዝ መሰረት ቢያንስ 80 ፍልስጤማዊያን መገደላቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጦር በደቡብ ጋዛ የሚገኙ ከስፍራው እንዲወጡ ድጋሚ ትዕዛዝ አስተላልፏል ። እስራኤል የጦር ማዘዣ ጣቢያ ላይ በማነጣጠር 19 ተዋጊዎችን መግደሏን አስታውቃለች።
ወታደሮቿን ቀደም ብለው ከፍልስጤም ተዋጊዎች ጋር ፍልሚያ ወደ ተደረገባቸው በእጅጉ የወደሙ ስፍራዎች እየመለሰች ያለችው እስራኤል፣ ነዋሪዎች ከስፍራዎቹ እንዲወጡ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።
በጋዛ ይኖር ከነበረው 2.3 ሚሊየን ህዝብ መካከል አብዛኛው 10 ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት ወቅት በተደጋጋሚ ተፈናቅሏል ። በመቶሺዎች የሚቆጠሩት ነዋሪዎች መጠነኛ ህዝባዊ አገልግሎት ባለባቸው ስፍራዎች ፣ ንጽህናቸው ባልተጠበቀ ድንኳኖች ውስጥ ተፋፍገው የሚገኙ አሊያም ቅዳሜ ዕለት እንደ ወደመው ባለ ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ናቸው ። ፍልስጤማዊያን በከበባ ውስጥ ባለው ግዛት ደህንነት እንደማይሰማቸው ገልጸዋል።
የአሁኑ ትዕዛዝ እስራኤል የሰብዓዊ አገልግሎት ቀጠና ብላ የሰየመቻቸውን የካንዩኒስ ስፍራዎች ያጠቃልላል። እስራኤል ከእነዚህ ስፍራዎች ሮኬቶች ተተኩሰዋል ብላለች ። እስራኤል ሀማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን በሲቪሎች መሀል በመሸሸግ እና ከመኖሪያ ስፍራዎች ጥቃቶችን በመፈጸም ትከሳለች።
የጋዛ ሁለተኛ ግዙፍ ከተማ የሆነው ካንዩኒስ በዚህ ዓመት መጀመሪያ በደረሰበት የአየር እና የምድር ጥቃት በእጅጉ የተንሰራፋ ውድመት ደርሶበታል። የቀደመው ትዕዛዝ ከተሰማ በኃላ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ባሳለፍነው ሳምንት ስፍራውን ለቀው ወጥተዋል።
የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለ10 ወራት ያህል በዘለቀው ጦርነት ፍልስጤማውያን የሟቾች ቁጥር ወደ 40,000 እየተቃረበ መሆኑን ገልጿል ። ከሟቾች መካከል ምን ያህሉ ተዋጊዎች እንደነበሩ አልገለጸም ። የእርዳታ ቡድኖች በግዛቱ ውስጥ ያለውን አስደንጋጭ የሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት በሚታገሉበት በአሁኑ ሰዓት ፣ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ደግሞ ረሃብ እንዳይከሰት አስጠንቅቀዋል።
ጦርነቱ የጀመረው በሀማስ የሚመሩ ታጣቂዎች በአውሮፓዊያኑ ጥቅምት 7 የእስራኤልን መከላከያ በመጣስ፣ በድንበር አቅራቢያ የሚገኙ አርሶ አደር ማህበረሰቦችን እና የጦር ሰፈሮችን በማጥቃት በአብዛኛው ሲቪል የሆኑ 1,200 ያህል ሰዎችን ገድለው ፣ ወደ 250 የሚጠጉ ሰዎችን ካፈኑ በኃላ መሆኑ ይታወሳል ( ዘገባው የአሶሼትድ ፕረስ ነው)።
መድረክ / ፎረም