በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
ምርጫ ቦርድ በተጭበረበረ ሰነድ ለህወሓት እውቅና ሰጥቷል ሲሉ አቶ ጌታቸው አቤቱታ አቀረቡ

ምርጫ ቦርድ በተጭበረበረ ሰነድ ለህወሓት እውቅና ሰጥቷል ሲሉ አቶ ጌታቸው አቤቱታ አቀረቡ


አቶ ጌታቸው ረዳ (ፎቶ ፋይል)
አቶ ጌታቸው ረዳ (ፎቶ ፋይል)


የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህ.ወ.ሓ.ት)፣ ትላንት “በልዩ ኹኔታ” የሰጠው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ፣ በተጭበረበረ ሰነድ ላይ ተመስርቶ መኾኑን ገልጸው ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ አቀረቡ።
ህወሓት በበኩሉ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ ምርጫ ቦርድ የሰጠው ውሳኔ ፓርቲው ካቀረበው ጥያቄ ጋራ የማይገናኝ እና ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ላቀረበው ጥያቄ መልስ የማይሰጥ በመኾኑ እንዳልተቀበለው አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጻፉት የተባለውና በክልሉ ቴሌቭዥን ጣቢያ ድረ ገጽ ላይ በሰፈረው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህ.ወ.ሓ.ት) “በልዩ ኹኔታ” የሰጠው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ በተጭበረበረ ሰነድ ላይ የተመሰረተ መኾኑን በመግለጽ አቤቱታ አሰምተዋል።
በሌላ በኩል፣ ማምሻውን መግለጫ ያወጣው ህወሓት፣ የምርጫ ቦርድ ምላሽ ፓርቲው ካቀረበው ጥያቄ ጋራ የማይገናኝ እና የፓርቲውውን ዳግም ሕጋዊ ሰውነት የሚመልስ ባለመኾኑ እንዳልተቀበለው ገልጿል።
በትግራይ ክልል በተጀመረውና ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በተሰፋፋው ጦርነት ምክኒያት ከፌደራል መንግሥቱ ጋራ ግጭት ወስጥ ገብቶ የነበረው ህወሃት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” በሚል ተፈርጆ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ሰርዞት ቆይቷል። ጦርነቱ በሰላም በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ህወሓት፣ ዳግም ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት፣ በተለያዩ ጊዜያት ለቦርዱ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል።
ምርጫ ቦርድ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ ፓርቲው በተደጋጋሚ ያቀረበውን ጥያቄ አስታውሶ፣ በቀድሞው ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011ም ኾነ በተሻሻለው ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሠረት፣ በዐመፃ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ሕጋዊ ሰውነቱ ለተሰረዘ ፓርቲ የቀድሞ ህልውናውን መልሶ የሚሰጥ ድንጋጌ አለመኖሩን ጠቅሶ፣ በድጋሚ የቀረበለትን የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ገልጿል፡፡
ኾኖም፣ በተሻሻለው ዐዋጅ፣ ኀይልን መሠረት ባደረገ የዐመፃ ተግባር ላይ የተሳተፈ የፖለቲካ ቡድን፣ ይህን ተግባሩን ማቆሙንና ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ በልዩ ኹኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ እንደሚችል መደንገጉን ጠቅሷል፡፡ በዚኽ መሠረት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ህወሓት፥ የዐመፃ ተግባር አቁሞ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በመግለጽ፣ በልዩ ኹኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ለቦርዱ ማረጋገጫ መስጠቱን እንዲሁም ህወሓት ለምዝገባ የሚያስፈልጉ የፓርቲ ሰነዶችን ማቅረቡን መግለጫው አውስቷል፡፡
በዚኽም፣ ህወሓት፣ በልዩ ኹኔታ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ እንዲሰጠው መወሰኑን ቦርዱ በመግለጫው አስታውቋል።
ይኽንን ውሳኔ ተቃውመው ደብዳቤ የጻፉት አቶ ጌታቸው ረዳ ፣ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው የህወሓት ማመልከቻ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው እና የተጭበረበረ ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል። ጥያቄውንም የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴው የማያውቀው ነው ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
"ለዚሁ ምዝገባ ብለን የፈረምነው ምንም ዓይነት ሰነድ ሳይኖር፣ ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው ከድርጅቱ አሰራር ውጪ የፈፀሙት ያልተገባ ተግባር መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን” ሲሉ ገልጸዋል።
"ቦርዱ የደረሰው ማመልከቻም ሆነ የፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና ፊርማ የያዘው የምዝገባ ጥያቄ ሰነድ ግለሰቦቹ እኛን ሳያስፈቅዱ የፈፀሙት መሆኑን እየገለጽን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለእነዚህ ግለሰቦች የሰጠው ምዝገባ በተጭበረበረ ማስረጃ በመሆኑ መልሶ እንዲመረምረው እንጠይቃለን” ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ የህወሓት ፅሕፈት ቤት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይቀበለው ባስታወቀበት ደብዳቤ፣ ቦርዱ ያስተላለፈው ውሳኔ ከፓርቲው ጥያቄ ጋራ የማይገናኝ መኾኑን አስታውቋል።
ህወሓት ጥያቄው ህጋዊ ሰውነት እንዲመልስለት እንጂ በተሻሻለው አዲሱ አዋጅ እዲመዘገብ እንደማይፈልግ ገልጿል::በፍትህ ሚኒስትር ህወሓት እንዲመዘገብ የተፃፈው ደብዳቤ ፓርቲው ያልጠየቀው እና ከህወሓት እውቅና ውጭ ነው ብሏል::
ህወሓት ያስገባው ማመልከቻም የፓርቲው መተዳደርያ ደንብ እና የአመራርች ስም ዝርዝር የገባ የተሰረዘው ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት እንጂ በተሻሻለው ሕግ እንዲመዘገብ አይደለም ብሏል መግለጫው::
የምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንደማይቀበለው ህወሓት ገልፆ ዝርዝር ይዘቶች በህወሓት ላይ የሚጭን ነው ብሎ በቀጣይ በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ተያያዥ ጉዳዮች ይፈፅማል ብሏል::
የፌደራሉ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል:: በጉዳዩ ላይ ከምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አስልተሳካም። ምላሻቸውን እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG