በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ምርጫ ቦርድ ህወሓትን “በልዩ ኹኔታ” መዘገበው


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህ.ወ.ሓ.ት)፣ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ “በልዩ ኹኔታ” መስጠቱን፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ህወሓት፣ ዳግም ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት፣ በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ ያቀረበውን ጥያቄ ያስታወሰው ቦርዱ፣ በቀድሞው ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011ም ኾነ በተሻሻለው ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሠረት፣ በዐመፃ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ሕጋዊ ሰውነቱ ለተሰረዘ ፓርቲ የቀድሞ ህልውናውን መልሶ የሚሰጥ ድንጋጌ አለመኖሩን ጠቅሶ፣ ቦርዱ በድጋሚ የቀረበለትን የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ገልጿል፡፡

ኾኖም፣ በተሻሻለው ዐዋጅ፣ ኀይልን መሠረት ባደረገ የዐመፃ ተግባር ላይ የተሳተፈ የፖለቲካ ቡድን፣ ይህን ተግባሩን ማቆሙንና ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ በልዩ ኹኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ እንደሚችል መደንገጉን ጠቅሷል፡፡ በዚኽ መሠረት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ህወሓት፥ የዐመፃ ተግባር አቁሞ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በመግለጽ፣ በልዩ ኹኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ለቦርዱ ማረጋገጫ መስጠቱን እንዲሁም ህወሓት ለምዝገባ የሚያስፈልጉ የፓርቲ ሰነዶችን ማቅረቡን መግለጫው አውስቷል፡፡

በዚኽም፣ ህወሓት፣ በልዩ ኹኔታ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ እንዲሰጠው መወሰኑን ቦርዱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በዛሬው ዕለት በልዩ ኹኔታ የተመዘገበው ህወሓት፣ በስድስት ወራት ውስጥ ጉባኤ እንዲያካሒድና መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጸድቅ፣ አመራሮቹንም እንዲመረጥ ቦርዱ መወሰኑን ገልጾ፣ የቅድመ ጉባኤ ዝግጅቱን ቦርዱ ለመከታተል እንዲችል፣ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማካሔዱ ከ21 ቀናት በፊት ቀኑን አስቀድሞ እንዲያሳውቀው የብሔራዊ ምርጫ ቦርዶ አሳስቧል፡፡

የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤው ከተካሔደ በኋላም፣ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመኾኑ ክትትል ለማድረግ መወሰኑን ቦርዱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG