በማሊ የሚገኙ አማጺያን የሃገሪቱን ወታደሮችና የዋግነር ቅጥረኛ ቡድን አባላትን ባለፈው ወር ሲገድሉ አስፈላጊዎን መረጃ እንደሰጠች ዩክሬን ማስታወቋን ተከትሎ፣ በኒዤር የሚገኘው ሁንታ ከትላንት ማክሰኞ ጀምሮ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጡን አስታውቋል።
የኒዤር ውሳኔ የመጣው ጎረቤት ማሊም ባለፈው እሁድ ግንኙነቷን እንዳቋረጠች ማስታወቋን ተከትሎ ነው። ዩክሬን የማሊን ውሳኔ “አርቆ የማያስብና ችኩል” ስትል ገልጻለች፡፡
ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔው የተከሰተው የዩክሬን ወታደራዊ የስለላ ቢሮ ቃል አቀባይ የማሊ አማጺያን ጥቃቱን ለመፈጸም አስፈላጊ ያሉትን መረጃ ከዩክሬን እንዳገኙ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው።
በሰሜን ማሊ የትዋረግ አማጺያን 84 የዋግነር ቅጥረኖችን እና 47 የማሊ ወታደሮችን ባለፈው ወር መግደላቸው ታውቋል።
ኒዤር ርምጃውን የወሰደችው ከማሊ መንግስት እና ሕዝብ ጋራ ያላትን አጋርነት ለማሳየት መሆኑን የመንግስት ቃል አቀባይ አብድራህማኔ አማዱ በሃገሪቱ ቴሌቭዥን ተናግረዋል።
በማሊ ለተፈጸመው ግድያ በቀጠናው የሚገኘው የዩክሬን አምባሳደር ድጋፍ እንደሰጡ ኤምባሲው በፌስቡክ ማስታወቁን ተከትሎ የሴኔጋል መንግስት አምባሳደሩን ጠርቶ አነጋግሯል።
መድረክ / ፎረም