በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር አንድ ወታደራዊ ሠፈርን አስረከበ


የኢትዮጵያ ጦር ከያዛቸው ወታደራዊ ሠፈሮች ውስጥ ማሃስ በተሰኘችው ከተማ ያለውን ሠፈር ለሶማሊያ ኃይሎች ሲያስረክብ (Photo by ATMIS)
የኢትዮጵያ ጦር ከያዛቸው ወታደራዊ ሠፈሮች ውስጥ ማሃስ በተሰኘችው ከተማ ያለውን ሠፈር ለሶማሊያ ኃይሎች ሲያስረክብ (Photo by ATMIS)

በአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ውስጥ በመሆን በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ከያዛቸው ወታደራዊ ሠፈሮች ውስጥ ማሃስ በተሰኘችው ከተማ ያለውን ሠፈር ዛሬ ለሶማሊያ ኃይሎች አስረክቧል።

ሂራን በተባለ ክልል፣ ከበለደወይን ከተማ 120 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘውና ዛሬ ለሶማሊያ ኃይሎች ተላልፎ የተሰጠው የጦር ሰፈር፣ የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ጦሩን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስ ባካሄደው ሶስተኛ ዙር የተፈጸመና፣ ለሶማሊያ ኃይሎች ተላልፎ የተሰጠ ስድስተኛው ወታደራዊ ሠፈር መሆኑን በሃገሪቱ የሚገኘው የኅብረቱ ልዑክ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኃይሎች በማሃስ ላለፉት 13 ዓመታት እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።

የፀጥታ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ እና አል-ሻባባን እንደሚፋለሙ የሶማሊያ ባለሥልጣናት መግለጻቸውን ልዑኩ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ ም/ቤት አሁን በሶማሊያ የሚገኘውን ልዑክ ከጥር ወር 2017 ዓ/ም ጀምሮ ተክቶ የሚሠራውን ሌላ አዲስ ልዑክ አስተዋውቋል። ም/ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ አዲሱ ኃይል “በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍና የማረጋጋት ልዑክ” ተብሎ እንደሚጠራም አስታውቋል። የአዲሱ ልዑክ መጠንም 11ሺሕ 900 እንደሚደርስና ይህም ከወታደሮች፣ ከፖሊስ እና ከሲቪሎች የተውጣጣ እንደሚሆን ታውቋል።

ልዑኩም በአፍሪካ ኅብረት በተቀመጠለት መመሪያ፣ እንዲሁም በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት ተልዕኮውን እንደሚፈጽም ኅብረቱ አስታውቋል።

በሶስተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ወታደሮችን ከሶማሊያ የማወጣት ሂደት፣ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ 2ሺሕ ወታደሮች እንደሚወጡም ታውቋል።

በሶማሊያ የሚገኘው የሕብረቱ የሽግግር ልዑክ ከ17 ዓመታት በፊት በእ.አ.አ 2007 የጀመረ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኬንያና ጂቡቲ የተውጣጡ ወታደሮችን ያቀፈ ነበር።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG