በኑሮ ውድነት ሳቢያ በናይጄሪያ ከተደረገው ተቃውሞ ጋራ በተያያዘ 21 ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ቡድኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
የመንግስትን ፖሊሲ እና ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን በመቃወም በሺሕ የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ባለፈው ሳምንት ተቃውሞ አድርገዋል። ተቃውሞው አሁን መቀዛቀዙ ተነግሯል።
የፀጥታ ኃይሎች ወደ ተቃዋሚዎቹ ጥይትና አስለቃሽ ጋዝ ሲተኩሱ መታዘባቸውን የኤኤፍፒ ዘጋቢዎች ከስፍራው አስታውቀዋል።
የፀጥታ ኃይሎች ለግድያው ተጠያቂ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
በቅድሚያ የሟቾቹ ቁጥር 12 እንደበር ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በናይጄሪያ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቢሮ ሃላፊ ኢሳ ሳኑሲ እንዳሉት፣ በሰሜናዊቷ ባዉቺ ግዛት ሰባት ተጨማሪ ሰዎች በመገደላቸው ቁጥሩ 21 ደርሷል። ሃያ አንዱም ተቃዋሚ ሰልፈኞች በጽጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን ሃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።
በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ጥይት መተኮሱን ያወገዙት ኃላፊው፣ የጸጥታ ኃይሎች ድርጊት እንዲመረመር ጠይቀዋል።
በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላት ናይጄሪያ ባለፈው ዓመት በፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ ተግባራዊ የሆነውን ተሃድሶ ተከትሎ ሃገሪቱ ለዘመናት ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡
መድረክ / ፎረም