በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ብዙ ሰው በነበረበት የተጨናነቀ የባህር ዳርቻ ላይ አልሻባብ ትላንት አርብ ምሽት ባደረሰው ጥቃት በትንሹ 32 ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች 63 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የሃገሪቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ ሜጀር አብዲፈታህ ኤደን አሊ ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ በአጥፍቶ ጠፊዎች የደረሰው በሃገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በርካቶች የሳምንቱ መጨረሻ ቀንን በባህርዳርቻው ለማሳለፍ በመምጣታቸው አካባቢው በሰዎች በተጨናነቀበት ሰዓት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በአገር ውስጥ የሚዲያ ድረ-ገጾች በለቀቋቸው የቪዲዮ ምስሎች በባህር ዳርቻው ወድቀው የሚታዩ የበርካታ የሞቱና ክፉኛ የቆሰሉ ሰዎችን ምስል አሳይተዋል፡፡
የመጀመርያው ፍንዳታ ከተፈፀመ በኋላ ሶስት የአልሸባብ ታጣቂዎች በባህር ዳርቻው አካባቢ የሚገኘውን የመመገቢያ እና መዝናኛ ህንፃን የወረሩ ሲሆ በኋላ ላይ በጸጥታ አካላት ሶስቱም የአልሻባብ አባላት መገደላቸውንና አራተኛው ደግሞ ራሱን ማጥፋቱን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሶማሊያ መንግስት የጸጥታ አካላትን ወዲያውኑ በስፍራው ማሰማራቱን የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ሃይሎች ለሃገሪቱ የመንግስት ሚድያዎችም በአራት ሰዓት ውስጥ ከበባውን መቆጣጠር መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የሞቃዲሾ ሆስፒታሎች በጥቃቱ የተጎዱትን ለማከም ደም እንዲለገስላቸውም ተማጽኖ እያቀረቡ ነው፡፡ የአልሻባብ ታጣቂ ቡድን በበኩሉ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
አልሸባብ በቤተሰብ ፣ ወጣቶችና በዲያስፖራዎች በሚዘወተረውን የሊዶ ባህር ዳርቻ ሬስቶራንቶችን እና ሆቴሎች ላይ በቀደሙት አመታትም ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸሙም ተነግሯል፡፡
መድረክ / ፎረም