በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኬንያ የዝንጀሮ ፈንጣጣ መታየቱ ከተረጋገጠ በኋላ በተጠንቀቅ ላይ ናት 


ፋይል - ይህ በብሔራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም (NIAID) የቀረበው ምስል በተበከለ ሕዋስ (ሰማያዊ) ውስጥ የተገኘ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ቀይ ) ስርጭት ያሳያል
ፋይል - ይህ በብሔራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም (NIAID) የቀረበው ምስል በተበከለ ሕዋስ (ሰማያዊ) ውስጥ የተገኘ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ቀይ ) ስርጭት ያሳያል

የኬንያ ባለስልጣናት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ መጋለጡ ከተደረሰበት አንድ ሰው ጋር የተገናኙና የተነካኩ ግለሰቦችን በማጣራት ላይ ናቸው።

ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ተጋልጧል የተባለው ሰው ከኡጋንዳ በኬንያ በኩል ወደ ሩዋንዳ እንደተጓዘ መታወቁ ስጋት ፈጥሯል፡፡

የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቫይረሱን ለመከላከል ግለሰቡ ተጉዞባቸዋል በተባለው በኬንያ እና ታንዛኒያ ድንበር አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ታይታ ታቬታ አውራጃ የጤና ባለሙያዎችን ልኳል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዋና ፀሃፊ ሜሪ ሙቶኒ የግንኙነት ክትትል እና ቁጥጥር አስፈላጊነትን አጉልተው በመግለጽ ፣ በዚህ ዙሪያ የሠለጠኑ የድንበር አካባቢ ጥበቃ ሠራተኞችን 32 ወደ ሚደርሱ አካባቢዎች ለቁጥጥር መካላቸውን ተናግረዋል፡፡

የዝንጀሮ ፈንጣጣ የምስራቅ፣ የመካከለኛው እና የምዕራብ አፍሪካ አካባቢዎችን እያጠቃ ነው፡፡

የበሽታው ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ ራስ ምታት እና መላውን ሰውነት የሚያም ፣ በቀጥታ ንክኪ ወይም በመተንፈሻ ጠብታዎችም ይተላለፋል።

የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከል እኤአ ከ 2022 ጀምሮ በ15 የአፍሪካ ሀገራት 1,450 የዝንጀሮ ፈንጣጣ ሞት የተመዘገበ ሲሆን ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ 14,250 ሰዎች መጋለጣቸው ተመዝግቧል፡፡ ከ እነዚህ መካከል 456 ሰዎች ሞተዋል።

ከ340,000 በላይ ሰዎች በሚኖሩባት የኬንዪቱ ታይታ ታቬታ አውራጃ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች፣ የቫይረሱ መስፋፋት ስጋት ስላደረባቸው ተጨማሪ የማህበረሰብ ግንዛቤ እና የጤና እርምጃዎችን እየጠየቁ ነው።

ቡሩንዲ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ሩዋንዳን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በሀገራቸው የዝንጀሮ ፈንጣጣ መከሰቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት አድርገዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG