በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በናይጄሪያው ተቃውሞ በትንሹ 13 ሰዎች ሞተዋል አለ 


በናይጀርያ አቡጃ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም.
በናይጀርያ አቡጃ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም.

በናይጄሪያ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በትንሹ 13 ሰዎች መሞታቸውን የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡ ተቃዋሚዎቹ የተገደሉት በጸጥታ ሃይሎች ነው ሲል ድርጅቱ ከሷል፡፡

በናይጄሪያ በሚገኙ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የመንግስትን ፖሊሲ እና የኑሮ ውድነትን በመቃወም አደባባይ በወጡበት ማግስት የሟቾች ቁጥርን አስመልክቶ እርስ በርስ የሚጋጩ ዘገባዎች እየወጡ መሆኑን የኤኤፍፒ ዘገባ ጠቅሷል፡፡

ዛሬ ዓርብ ቢያንስ አምስት የናይጄሪያ ግዛቶች በሰአት እላፊ ስር ቆይተዋል፡፡

በዋና ከተማዋ አቡጃ የጸጥታ ሃይሎች ለሁለተኛ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸውን በስፍራው የሚገኘው የኤኤፍፒ ዘጋቢ ተናግሯል።

የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ቦላ ቲኑቡ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረጉት የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ የነዳጅ ድጎማን ማስቀረቱ እና የገንዘብ ልውውጡን ወደ ነጻ ገበያ መቀየሩ በረጅም ጊዜ ሂደት ኢኮኖሚውን ያሻሽላል ብለው ተናግረው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር በከፍተኛ የዋጋ ንረት እና የኒያራን የምንዛሬ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ የኑሮ ውድነት ቀውስ አምጥቶብናል በማለት ብዙዎች ናይጄሪያዊያን መንግሥታቸውን ይወነጅላሉ፡፡

“በናይጄሪያ መጥፎ አስተዳደር ያብቃ!” የሚል ስያሜ የተሰጠው የተቃውሚዎቹ የንቅናቄ ዘመቻ በኢንተርኔት በርካታ የተከታዮች ድጋፍ አግኝቷል፡፡

የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ደግሞ በቅርቡ በኬንያ አዲሱን የታክስ ህግ በማስቀየር የተደረጉ የሁከትና የብጥብጥ ሰልፎችን ተመሳሳይ መንገድ መከተል መሞከሩ አደገኛ መሆኑን አስጠንቅቀዋል፡፡

አመጹ ያስተሳሰራቸው ናይጄሪያውያን ተቃዋሚ የሲቪል ማህበራት ቡድኖች ከመንግስት የተሰጠውን ማስጠናቀቂያ ችላ በማለት በመጭዎቹ ቀናት የተቃውሞ ሰልፎችን እንደሚያካሂዱ ዝተዋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደዘገበው የጸጥታ ሃይሎች በዋና ከተማዪቱ አቅራቢያ በሱሌጃ 6 ሰዎችን፣ በሰሜን ምስራቅ ማይዱግሪ ከተማ አራት እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው ካዱና ከተማ ሶስት ሰዎች መግደላቸውን አስታውቋል፡፡

የሀገሪቱ ፖሊስ አዛዥ መኮንኖች ፖሊሶች በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል የሚለውን ክስ አስተባብለዋል።

ናይጄሪያውያን 40 በመቶ በጨመረው የምግብ ግሽበት እና በሶስት እጥፍ በናረው የነዳጅ ዋጋ የተነሳ ለከፍተኛ ወጭና የኑሮ ውድነት ተዳርገዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG