በተለያዩ የናይጄሪያ ከተሞች በብዙ ሺዎች የተቆጠሩ ሰዎች ዛሬ ሐሙስ ጸረ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ አሽመድማጅ የሆነው የዋጋ ግሽበት እና የገንዘቧ ዋጋ ማሽቆልቆሉ ባስከተለው የኑሮ ውድነት ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
በዋና ተማዋ አቡጃ እና በሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ ካኖ በመንግሥት ህንጻዎች ደጃፍ እሳት ለማቀጣጠል የሞከሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ፖሊስ በአስለቃሽ ጢስ በትኗል፡፡
በንግድ መዲናዋ ሌጎስም ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሙስናን የሚያወግዙ ሰሌዳዎች እና የሀገሪቱን ባንዲራ ይዘው ደወል እየደወሉ እና እየዘመሩ ወደመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሄዱ ሲሆን ብዛት ያላቸው የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎች ጎዳናዎች መሰማራታቸው ተዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ቦላ ቲኑቡ እ አ አ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረጉት የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ የነዳጅ ድጎማን ማስቀረቱ እና የኒያራን የምንዛሬ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉ የኑሮ ውድነት ቀውስ አምጥቶብናል በማለት ብዙዎች ናይጄሪያዊያን ይወነጅላሉ፡፡
ሰሞኑን ኬኒያ ውስጥ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ፕሬዚደንቱ የታክስ ጭማሪ ህጉን እንዳይፈርሙ ማድረጉን ተከትሎ የተበረታቱ ናይጄሪያዊያን አንቂዎች ባለፉት ሳምንታት በኢንተርኔት አማካይነት የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ አደራጆች የሰልፉ ዓላማ የምጣኔ ሐብት ችግሮቹን እና ስር የሰደዱ ሥርዓታዊ ችግሮች በሆኑት እንደ ሙስና እና የፕሬስ ነጻነት በመሳሰሉት ጉዳዮች ተቃውሞ ለማሰማት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የናይጄሪያ ፓርላማ አባላት ባለፈው ሳምንት የፌዴራል መንግሥቱ ሠራተኞች ደመወዝ ከ30 ሺህ ናያራ ከእጥፍ በላይ በማሳደግ 70 ሺህ ናያራ 43 ዶላር ገደማ እንዲሆን ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ በዚህ ሳምንት ህጉን የፈረሙት ቢሆንም አገር አቀፍ ተቃውሞውን ለማብረድ ብዙም አልረዳም፡፡
የናይጄሪያ የሀይማኖት መሪዎች እና ሌሎችም ማህበረሰባዊ ቡድኖች “በኬኒያው የተቃውሞ ሰልፍ እንደሆነው ሁከት ይቀሰቀሳል” በሚል ፍራቻ የተቃውሞ ሰልፉ እንዳይካሄድ ለማግባባት ሞክረው እንደነበረም ተዘግቧል፡፡
የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች በበኩሉ የናይጄሪያ መንግሥት ከተቃውሞ ሰልፎቹ አስቀድሞ የሰጣቸው መግለጫዎች የኅይል እርምጃ እንደሚወስድ የሚጠቁሙ መሆናቸውን ገልጾ አስጠንቅቋል፡፡
መድረክ / ፎረም