በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢራን ለተገደሉት የሀማስ መሪ የአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዐት አካሄደች


በኢራን የሀማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬ የአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት (AP Photo/Vahid Salemi)
በኢራን የሀማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬ የአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት (AP Photo/Vahid Salemi)

ኢራን በዋና ከተማዋ ቴህራን ለተገደሉት የሀማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬ የአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት አካሂዳለች፡፡ የሃማሱ መሪ መገደል ክልላዊ ግጭት ያስከትላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡

ዛሬ ሐሙስ በተከናወነው የአስከሬን ሽኝት ላይ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ እና አዲሱ ፕሬዚደንት ማሱድ ፔዚሽኪያን ተገኝተዋል፡፡

ኢስማኤል ሃኒዬ ወደ ቴህራን የተጓዙት በአዲሱ ፕሬዚደንት በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ሃማስ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን መቀመጫቸው በነበረችው በካታር ነገ ዓርብ እንደሚፈጸም አስታዉቋል፡፡

ዛሬ ሞንጎሊያ ጉብኝት ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የሃኒዬን ግድያ በቀጥታ ሳያነሱ በመካከለኛው ምሥራቅ መረጋጋት እንዲሰፍን ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ በበኩላቸው ትላንት ረቡዕ ባወጡት መግለጫ የሀኒዬ መገደል እንዲሁም እስራኤል ቤይሩት ውስጥ የሄዝቦላ የተዋጊ አዛዥን መግደሏ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ውጥረቱን በአደገኛ ሁኔታ የሚያባብስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስራኤል ከትላንት በስተያ ማክሰኞ ከፍተኛ የሄዝቦላ አዛዥ ፉአድ ሹኩር ቤይሩት ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ገድላለች፡፡ እ አ አ ሐምሌ 13 ቀን ደቡባዊ ጋዛ ኻን ዩኒስ ውስጥ ባደረሰችው የአየር ጥቃት የሃማስን ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ መሐመድ ዴይፍን መግደሏንም ዛሬ ሐሙስ አረጋግጣለች፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ “በማናቸውም ግንባር በኛ ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት የሚሰነዝር ከባድ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉ ትላንት የተናገሩ ሲሆን የኢስማኤል ሃኒዬን ግድያ ግን አላነሱም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ኃይሎች ጋዛ ኻን ዩኒስ ላይ የአየር ድብደባ መቀጠላቸውን ራፋህ እና ማዕከላዊ ጋዛ ውስጥም ወታደሮቻቸው እያጠቁ መሆናቸውን የእስራኤል የጦር ኅይል አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG