የዓለም ባንክ፣ ትላንት ማክሰኞ ለኢትዮጵያ በድጋፍ እና በብድር መልክ የፈቀደውን 1ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር ያካተተ ተጨማሪ የበጀት ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ዛሬ አስታውቀዋል፡፡
ተጨማሪው በጀት፣ የዋጋ ንረት ተጽእኖን ለመቀነስ ለሚወሰዱ የደመወዝ ጭማሬ እና ለሌሎች ድጎማዎች እንደሚውልም ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
ምክር ቤቱ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል በተደረሰው የብድር ስምምነት ላይ ውይይት አድርጎ አጽድቆታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ እሑድ፣ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገውን፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሚደግፍ ያሳወቀው የዓለም ባንክ ከለቀቀው ገንዘብ ውስጥ በብድር መልክ የተገኘውን 500 ሚሊዮን ዶላር ለማጽደቅ፣ በአፈ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ዛሬ ባካሔደው ውይይት ላይ ከምክር ቤት አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነሥተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ የሚያስከትለውን የኑሮ ውድነት የተመለከተው ከጥያቄዎቹ መካከል ይገኝበታል፡፡ ለጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፣ “መንግሥት ሪፎርሙ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቋቋም በቂ ዝግጅት አድርጓል፤” ብለዋል፡፡ የዋጋ ንረት ተጽእኖን ለመቀነስም፣ ለመንግሥት ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሬ እና ለተለያዩ ድጎማዎች የሚውል ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብ አቶ አሕመድ አስታውቀዋል፡፡
ለደመወዝ ጭማሬ እና ለሌሎች ድጎማዎች ለማዋል፣ መንግሥት ለምክር ቤቱ ከሚያቀርበው የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ውስጥ፣ የዓለም ባንክ አካል ከኾነው ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል የተገባው ገንዘብ እንደሚገኝበት ተናግረዋል፡፡
የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ፓርቲ የምክር ቤት ተመራጭ የኾኑት አቶ አበባው ደሳለው፣ ይፋ የኾነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅት አንጻር ምን ያህል ተገቢ እንደኾነ ጥያቄ አንሥተዋል፡፡
አቶ አሕመድ ሽዴ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፣ የሰላም ዕጦቱ የሚኖረውን ተጽእኖ ባያነሡም፣ ማሻሻያው “የአገሪቱን ዕዳ የሚያቃልል ነው፤” ብለዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሽግግር ወቅት እክሎችን እንዲሁም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ መንግሥት ስለሚወስዳቸው ርምጃዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ነገ ኀሙስ፣ ሐምሌ 24 ቀን ማብራሪያ እንደሚሰጡም አቶ አሕመድ ሺዴ ተናግረዋል፡፡
ከዓለም ባንክ ጋራ በተደረሰው የብድር ስምምነት ላይ ውይይት መደረጉን ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤቱ፣ የብድር ስምምነቱን በአንድ ተቃውሞ እና በአንድ ድምፀ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል፡፡
የዓለም ባንክ፣ ትላንት ረቡዕ ያጸደቀውን 1ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ፣ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በድጋፍ፣ በብድር እና በዕዳ ሽግሽግ በአጠቃላይ 16ነጥብ6 ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ እንደሚያቀርብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
የዓለም ባንክንና ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም ጨምሮ ከዓለም የገንዘብ ተቋማት የሚገኙ ድጋፎች ግን፣ የውጭ ምንዛሬ ተመንን ገበያ መር ማድረግን ጨምሮ በጥብቅ የኢኮኖሚ ሪፎርም ቅድመ ኹኔታዎች የታጀቡ ናቸው፡፡
የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ፣ ባንኮች የብርን የመግዛት ዓቅም ማዳከማቸውን በመቀጠል፣ በዛሬው ዕለት የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ ሁለት ጊዜ ለውጦችን በማሳየት በንግድ ባንክ ከ80 ብር በላይ ተተምኖ ሲውል፣ ከግል ባንኮች የአንድ ዶላር ዋጋን ከ81 ብር በላይ የተመኑ አሉ፡፡
የመንግሥት የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ርምጃ፣ ወቅታዊ እንዳልኾነና የተለያዩ ኢኮኖሚ ነክ ቀውሶችን ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳስቡ የዘርፉ ተንታኞች አሉ፡፡
በአንጻሩ፣ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች በማገልገል እና በአማካሪነት የሚታወቁት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው፣ ዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ፣ ባለፉት ሁለት ቀናት በድምሩ 20 ቢሊዮን ዶላር፣ ለኢትዮጵያ ፈንድ ለማድረግ ቃል መግባታቸው፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው፤ ብለዋል፡፡
ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ መጠን እንደሚቀይር እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
መድረክ / ፎረም