በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ ጀኔራል ቡርሃን ከድሮን ጥቃት ተረፉ


ፋይል፡ የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ ቡርሀን በሱዳን ካርቱም ኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደ ስነስርዓት ላይ ንግግር እያደረጉ ያሳያል
ፋይል፡ የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ ቡርሀን በሱዳን ካርቱም ኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደ ስነስርዓት ላይ ንግግር እያደረጉ ያሳያል

የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታህ ቡርሀን ዛሬ ረቡዕ ከተቃጣባቸው የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት መትረፋቸውን የሀገሪቱ ጦር አስታወቀ፡፡

ቡርሃን የተረፉት በምስራቅ ሱዳን በተካሄደው የጦር ሠራዊት ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የ5 ሰዎች ህይወት ካለፈበት የድሮን ጥቃት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እንደተፈጸመ የተገለጸው ጥቃት የተካሄደው በገበይት ከተማ ሲካሄድ የነበረው የምርቃት ስነ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑንም ሠራዊቱ ጨምሮ ገልጿል።

ቡርሃን በጥቃቱ ጉዳት ያልደረሰባቸው መሆኑን የወታደራዊ ቃል አቀባያቸው ሌተናል ኮሎኔል ሀሰን ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ብዙ ሰዎች አቧራማ በሆነው መንገድ ሲሮጡ እና ሌሎቹም ሰው አልባው አውሮፕላኑ ሲመታ ወደ ሰማይ አንጋጠው ሲመለከቱ በአል አረብ ቴሌቭዥን ላይ የወጣው የቪዲዮ ምስል አሳይቷል፡፡

የሱዳን ጦር ኃይሎች በፌስቡኩ ገጹ ላይ ያወጣው የቪዲዮ ምስል ደግሞ፣ ከጥቃቱ በኋላ በፈገግታ ቆመው የሚታዩት ቡርሃንን የከበቡ ሰዎች ደስታቸውን ሲገልጹ አሳይቷል፡፡

ስለ ተቃጣው የግድያ ሙከራ ጥቃት የፈጥኖ ደራሹ ጦር እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም፡፡

ሱዳን በጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በግጭቱ በርካቶች ሲገደሉ፣ ከ4.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG