በደቡባዊ ህንድ ትላንት ማክሰኞ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት በትንሹ 151 ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች ዛሬ ረቡዕ በጭቃዎችና ፍርስራሾችን መካከል ተጎጂዎችን እያፈላለጉ ነው፡፡
በኬረላ ግዛት ዋያናድ አውራጃ ውስጥ ትላንት ማክሰኞ ጧት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው የጭቃ እና የውሃ ጎርፍ በሻይ ልማት ወደ ታወቁ ግዛቶች እና መንደሮች ውስጥ ዘልቆ በመግባት ጉዳት አድርሷል፡፡
በአደጋው ከሞቱት ሌላ 186 ሰዎች መቁሰላቸው፣ ቤቶች መውደማቸው፣ ዛፎች መነቃቀላቸው እና ድልድዮች መፍረሳቸው ተነገሯል፡፡
በአደጋው 187 ሰዎች የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን 77 አስከሬኖች ተለይተው በአብዛኛው ለዘመዶቻቸው መተላለፋቸውን የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ከ300 በላይ የነፍስ አድን ሠራተኞች በተዘጉ መንገዶች እና ባልተረጋጋው መሬት ሳቢያ ያጋጣመቸው መሰናክል ጥረታቸውን እያደናቀፈው መሆኑን ተገልጿል፡፡
ከአደጋው ጋር በተያያዘ ከ 8,300 በላይ ሰዎች ወደ 82 የመንግስት የእርዳታ ካምፖች የተወሰዱ ሲሆን ምግብ እና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ታድሏቸዋል ።
ባለስልጣናት ወደ 20,000 ሊትር የሚደርስ የመጠጥ ውሃ የያዙ ተሽከርካሪዎችን ወደ አካባቢው በመላክ ጊዜያዊ ሆስፒታሎችን በማቋቋም ላይ እንደሆኑ ዘገባው አመልክቷል፡፡
መድረክ / ፎረም