የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን ያቀረበበትን ክስ፣ “ስም የማጥፋት ሥራ ነው” ሲል የተቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አቭዬሽኑ የበረራ እገዳ ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቋል፡፡
የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን፣ በአገሪቱ ጋዜጣ ላይ ታትሞ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በተሰራጨ የእግድ ትእዛዙ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የተለያዩ ክሶችን አቅርቦ፣ አየር መንገዱ ወደ ኤርትራ የሚያደርገው በረራ፣ ከመጪው መስከረም 20 ቀን ጀምሮ እንዲቋረጥ መወሰኑ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ትላንት ሰኞ፣ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ የኤርትራ ባለሥልጣናት “ውሳኔያቸውን እንደገና ያዩታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤” ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት፣ ካለፈው ዓመት የ14 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ገቢ ማግኘቱንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከመጪው መስከረም 20 ቀን ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚያደርገው ኹሉም በረራ እንዲቋረጥ የእግድ ውሳኔ ያሳለፈበትን ክስ እንደማይቀበለው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ፣ ትላንት ሰኞ፣ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ከጋዜጠኞች ለተነሡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ላይ፣ የኤርትራ ሲቪል አቭዬሽን፣ “ሐዳስ ኤርትራ” በተሰኘ የአገሪቱ ጋዜጣ ላይ ታትሞ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በተሰራጨ የእግድ ትእዛዙ፣ በአየር መንገዱ ላይ ያቀረባቸውን የተለያዩ ክሶች “አንቀበልም” ብለዋል፡፡
ኤርትራውያን መንገደኞች ወደ አገራቸው ሲጓዙ የሚይዙት ሻንጣ፣ ከአውሮፕላኑ ዓቅም በላይ ከመኾኑ ጋራ ተያይዞ፣ ሻንጣዎች ዘግይተው ይደርሱ እንደነበር የገለጹት አቶ መስፍን፣ “ይህ ጉዳይ አስቀድሞ መፍትሔ ያገኘ ነው፤” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር፣ ሰላም፣ ንግድ እና ቱሪዝም እንዲጠናከር፣ ባለፉት ዓመታት ሚናውን ሲጫወት ቆይቷል፤ ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን፣ ኤርትራ የእገዳ ውሳኔዋን መልሳ እንድታጤነው ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ኤርትራ ውስጥ አለ የተባለውን የአየር መንገዱን ውዝፍ ገንዘብ ማስመለስ በተመለከተ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ለተጠየቁት አቶ መስፍን በሰጡት ምላሽ፣ አየር መንገዱ በዶላር እና በአገሪቱ መገበያያ ናቅፋ ገንዘብ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ “ዶላሩን እያመጣን ነው፤ ከዚኽ ጋራ የተገናኘ ክልከላም የለም፤ በኤርትራ ገንዘብ ያለው ግን ለዓመታት የቆየና በቀላሉ የሚወጣ አይደለም፤” ካሉ በኋላ፣ “በሁለቱ ሀገራት ንግግር ተደርጎ በስምምነቱ መሠረት የሚወጣ ይኾናል፤” ብለዋል፡፡
“ወታደሮችን በማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ አሠራርን ትጥሳላችኹ፤” በሚል አየር መንገዱ ለሚቀርብበት ውንጀላም፣ አቶ መስፍን፣ እንደ ንግድ ተቋም በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት ብቻ የሚከናወን ያሉትን ወታደሮችን ከቦታ ቦታ የማንቀሳቀስ ተግባር ስለመኖሩ አስረድተዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱንና ከዚኽም ከፍተኛው ቁጥር ከመንገደኞች ትራንስፖርት የተገኘ መኾኑን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አየር መንገዱ፣ አምስት ተጨማሪ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በመጨመር፣ የዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ጠቅላላ ቁጥር 139 አድርሷል፤ ያሉት አቶ መስፍን፣ በሀገር ውስጥ ደግሞ ባለፈው ዓመት ወደ ሦስት ከተሞቸ መብረር እንደጀመረና ከዐዲስ አበባው ውጭ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹን 21 ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
መድረክ / ፎረም