በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የሚመለከቱ የለውጥ እቅዶችን ይፋ አደረጉ


ፋይል - የጠቅላይ ፍርድ ቤት ህንፃ ፣ ዋሽንግተን፡ ሰኔ 20 ቀን 2024 ዓ.ም.
ፋይል - የጠቅላይ ፍርድ ቤት ህንፃ ፣ ዋሽንግተን፡ ሰኔ 20 ቀን 2024 ዓ.ም.

ፕሬዝዳንት ባይደን የዩናይትድ ስቴትስን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስመልክቶ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቁ የነበሩ የለውጥ ሀሳቦችን አቀረቡ፡፡

የዲሞክራቲክ ፓርቲው ፕሬዝዳንት የሀገሪቱ ምክር ቤት የዘጠኙ ዳኞችን የሥልጣን ጊዜ ገደብና የስነምግባር ድንጋጌ እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን አያይዘውም ሕግ አውጪዎች የፕሬዚዳንቱን ያለመከሰስ መብት የሚገድብ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲያፀድቁ ግፊት እያደረጉ መሆናቸው ተመልክቷል።

ዋይት ሀውስ ባይደን በፍርድ ቤቱ እንዲኖር ያቀዱትን ለውጦች በዝርዝር አስቀምጧል።

ይሁን እንጂ የባይደን እቅድ ሊካሄድ 99 ቀናት ብቻ በቀሩት የምርጫ ጊዜ ውስጥ፣ በተከፋፈለው የሀገሪቱ ምክር ቤት ዘንድ የመጽደቅ እድሉ አነስተኛ ነው ተብሏል።

ዲሞክራቶች ግን ብርቱ የቅርብ ፉክክር በሚታይበት የምርጫ ውድድር የመራጮችን ጠንካራ ትኩረት እንደሚስብ ተስፋ አድርገዋል፡፡

በይፋ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ውድድሩን “በነጻነት እና በሁከት መካከል ያለ ምርጫ” በሚል መስለውታል።

በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አስተያየት መስጫ ላይ የሰፈረው የባይደን አስተያየት ለተቋማት ክብር አፅንዖት ሰጥቷል፡፡

"አሁን ያለው ሁኔታ ህዝቡ በፍርድ ቤት ላይ ያለውን እምነት ያሳጣል" ሲሉም ባይደን በጽሁፋቸው ተከራክረዋል።

የባይደን እቅድ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ዳኞች የህይወት ዘመን አገልግሎት ወደ 18 ዓመት ዝቅ እንዲደረግ እና ፕሬዚዳንቱ በየሁለት ዓመቱ አዳዲስ ሹመቶችን እንዲያካሂድ ምክር ቤቱን ይጠይቃል፡፡

ባይደን በፕሬዚዳንት ያለመከሰስ መብት ላይ የተሰጠውን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን ለመቀልበስ የሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትረምፕ የለውጥ ጥረቶቹ በምርጫው ውስጥ ጣልቃ ለመግባት እና የፍትህ ስርዓቱን ለማጥቃት ኢዲሞክራሲያዊ ሙከራ ነው ሲሉ ተችተውታል።

“ዴሞክራቶች የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን፣ እኔን እና የተከበረውን ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በማጥቃት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት እና የፍትህ ስርዓታችንን ለማጥፋት እየሞከሩ ነው፡፡ ለፍትሃዊ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶቻችን መታገል እና አገራችንን መጠበቅ አለብን" ሲሉ ትረምፕ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ “ትሩዝ ሶሻል” በተሰኘው ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG