የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከሚገኝ ሚስጥራዊ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ስልጠና ሲወስዱ የተገኙ ያሏቸውን 95 ሊቢያውያን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ፡፡
ከጆሐንስበርግ በስተሰሜን ምስራቅ 360 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘውን ምፑማላንጋ ክፍለ ግዛት ዋይት ሪቨር በተባለ አካባቢ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ላይ ያለውን ይህን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ወርሮ ሰዎቹን ማሰሩን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የደቡብ አፍሪካ የብሔራዊ ፖሊስ ሠራዊት ቃል አቀባይ አትሌንዴ ማቲ ዛሬ በኤክስ ገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ ሊቢያውያኑ ደቡብ አፍሪካ የገቡት የደህንነት ጥበቃ ስልጠና ለማግኘት የትምህርት ቪዛ ተቀብለው መሆኑን እንደተናገሩ አመልክተዋል፡፡ ሆኖም እየወሰዱ ያሉት ወታደራዊ ስልጠና መሆኑን ፖሊስ ተከታትሎ ደርሶበታል ብለዋል፡፡
ኒውዝሩም አፍሪካ ቴሌቪዥን ሰዎቹ የተያዙባቸውን ወታደራዊ ካምፕ የመሰሉ አረንጓዴ ድንኩዋኖች ያሉበትን ምስል ማሳየቱን አሶሼትድ ፕሬስ አውስቷል፡፡
መድረክ / ፎረም