ዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ግለቷ እየጨመረ እና ሁላችንንም በይበልጥ ለአደጋ እያጋለጠ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ አስጠነቀቁ፡፡
በዓለም አየር ግለት የተነሳ በየዓመቱ ቁጥራቸው ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎች እንደሚሞቱ የገለጡት ዋና ጸሐፊው ለአየር ግለቱ መባባስ ምክንያቱ ከቅሪተ አካል የሚገኙ ነዳጆች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
“በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ከሃምሳ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለሚያሻቅብ እና ገዳይ ለሆነ የአየር ግለት እየተጋለጡ ናቸው” ብለዋል፡፡
ባለፈው ዕሁድ በዓለም ላይ ከምንጊዜውም የበለጠ የአየር ግለት ከተመዘገበ በኋላ በማግሥቱ ሰኞ ከዚያ የባሰ ንዳድ ተመዝግቧል፡፡ ሙቀቱ ከዕለት ወደ ዕለት በተከታታይ እየተባባሰ ሲሆን ሳይንቲስቶች ያለፉት ተከታታይ 13 ወራት ከምንግዜውም የከፋ የአየር ግለት የተመዘገበባቸው እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ የከተሞች ሙቀት ከአጠቃላዩ አማካይ የዓለም የአየር ግለት የበለጠ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
እ አ አ በዚህ 2024 ዓም በአስከፊ ንዳድ ምክንያት ህንድ እና የአፍሪካ የሳህል አካባቢ ሀገሮች ብዛት ያላቸ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ባለፈው ወር ሳውዲ አረቢያ ውስጥ 1300 የሐጂ ተጓዦች ሞተዋል፡፡ በቅርቡም አውሮፓ፡ ዩናይትድ ስቴትስ እና እስያ ውስጥ ከባድ ሙቀት ተከስቷል፡፡
በዓለም የጤና ድርጅት እና በዓለም የሚቴዎሮሎጂ ድርጅት መሠረት በ57 ሀገሮች ያለው ከአየር ግለት ተያያዥ የጤና አደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ቢሻሻል በየዓመቱ ወደ 100ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት ለማትረፍ እንደሚቻል መናገራቸውን ዋና ጸሐፊ ጉቴሬዥ አመልክተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም