የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ዛሬ በዋይት ሃውስ ተቀብለው ሲያነጋግሩ፤ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሐማስ ላይ እያካሄደች ያለችው ጦርነት ‘ልዩ ትኩረት ያገኛል’ ተብሎ ይጠበቃል።
አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ባለሥልጣን በትላንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ባይደን “ለእስራኤል ደህንነት መጠበቅ ያላቸውን የማያወላውል ድጋፍ” እንደሚገልጹ እና በውይይታቸውም ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ ካሉት በኢራን የሚደገፉት እንደ ሃማስ፣ ሂዝቦላ እና የየመኑ ሸማቂ ቡድን ሁቲ በእስራኤል ደህንነት ላይ የደቀኑትን ስጋት አስመልክቶም ይወያያሉ ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች በጋዛ ካለው ሰብአዊ ሁኔታ በተጨማሪ ለጦርነቱ ማብቂያ ለማበጀት ከተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ በተያዘው ጥረት፣ ጋዛ ውስጥ በሃማስ ተይዘው የሚገኙት ታጋቾች ስለሚፈቱበት ሁኔታ፣ እስራኤል ፍልስጤማውያን እስረኞችን ስለምትለቅበት እና እንዲሁም ጋዛ ውስጥ ለፍልስጤማውያን የሚደርስ የሰብአዊ ርዳታ በሚጨምርበት መንገድ ዙሪያ ይወያያሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ከግብፅ እና ከኳታር ጋራ በመተባበር በመሥራት ላይ የምትገኘው የተኩስ አቁም ድርድር ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እስራኤል እና ሃማስ በየበኩላቸው ከሚጠይቋቸው መጣጣም ያልቻሉ ፍላጎቶች የተነሳ ለወራት መራዘሙ ይታወሳል።
ኔታንያሁ ለመጪው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የፓርቲያቸው ዕጩ ለመሆን ግንባር ቀደም ከሆኑት ከምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ ጋራም የሚገናኙ ሲሆን የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ነገ አርብ ተቀብለው እንደሚያነጋግሯቸው ተመልክቷል፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ደጃፍ በሺዎች የተቆጠሩ የፍልስጤማውያን ደጋፊውዎች እና ጦርነቱን የሚቃወሙ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፍ ከሃምሳ በላይ ዲሞክራት የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት በትላንቱ ንግግራቸው ላይ ሳይገኙላቸው ቀርተዋል፡፡ ይሁን እና ኔታንያሁ ግን ጋዛ ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንደሚደረስ እንደሚተማመኑ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ለወራት የዘለቀው እና አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ድርድር እየተሳካ ስለመሆኑ የሰጡት ፍንጭ የለም፡፡
የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬዝደንት ባይደንን ለእስራኤል ከሃማስ ጋራ በምታካሂደው ጦርነት የምትዋጋበት ብዛት ያለው የጦር መሣሪያ በፍጥነት በመላክ ስላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል። ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን የዩናይትድ ስቴትስን ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም በማዛወራቸው እና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠታቸው የቀድሞውን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕንም አመስግነዋቸዋል፡፡
መድረክ / ፎረም