በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምያንማር ተፋላሚ ወገኖች ወታደራዊ ጦር ሰፈርን ተቆጣጥሬያለሁ በሚል እየተወዛገቡ ነው


ፋይል፡ የምያንማር ሰሜናዊ ሻን ግዛት ላሺዮ ከተማን አጠቃላይ እይታ ያሳያል፣ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም.
ፋይል፡ የምያንማር ሰሜናዊ ሻን ግዛት ላሺዮ ከተማን አጠቃላይ እይታ ያሳያል፣ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም.

የምያንማሩ ወታደራዊ ጁንታ እና አንድ ህዳጣን የጎሳ ታጣቂ ቡድን ተዋጊዎች በየፊናቸው፤ ለበርካታ ቀናት ያካሄዱትን ውጊያ ተከትሎ በሰሜናዊው የሻን ክፍለ ግዛት የሚገኘውን ወታደራዊ ጦር ሰፈር እና አንዲት ከተማ መቆጣጠራቸውን እየተናገሩ ነው።

ከሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የጎሳ ታጣቂ ቡድኖች በወታደራዊ ጁንታ ኃይሎች ላይ በጋራ የከፈቱትን ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ፤ የጦሩ የሰሜን ምስራቅ እዝ መቀመጫ የሆነችው የላሺዮ ከተማ በውጊያው ክፉኛ ስትናወጥ ሰንብታለች።

የምያንማር ብሄራዊ ዲሞክራቲክ ጥምረት ጦር የተባለው ቡድን የሚቆጣጠረው የዜና ምንጭ ትላንት ማለዳ ላይ እንደዘገበው፡ በላሺዮ የሚገኘውን የወታደራዊ ጦር ሰፈር ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠሩም ባሻገር የ150 ሺህ ሕዝብ መኖሪያ የሆነችውን የላሺዮ ከተማን ጨምሮ ከእጁ አስገብቷል።

የጁንታው ቃል አቀባይ ዛው ሚን ቱን በበኩላቸው ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ‘የጦር ካምፑን እና ከተማይቱን ተቆጣጥሬያለሁ’ የሚለው የቡድኑ ገለጣ "እውነት አይደለም" ብለዋል።

"አማፂያኑ የላሺዮ ከተማ ዳርቻ አካባቢዎችን ዘልቀው ቢገቡም፤ የጸጥታ ኃይሉ ተከታሎ እየመነጠራቸው ነው" ብለዋል። ይሁን እንጂ ‘ጦሩ እየወሰደ ነው’ ያሉትን እርምጃ አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ትላንት ማለዳ ላይ በማሕበራዊ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨ እና ‘ላሺዮ ውስጥ የተነሳ ነው’ የተባለ የቪዲዮ ምስል ወታደር የማይታዩባቸውን ጭር ያሉ መንገዶች ያሳያል።

የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘጋቢዎች የዲጂታል ዘዴ ተጠቅመው ባደረጉት መልክአምድር ጠቋሚ ግምገማ መሰረት ቪዲዮው የተነሳበትን ሥፍራ ወታደራዊ ጦር ሰፈሩ ከሚገኝበት ሁለት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ያለ አንድ የከተማይቱ ሥፍራ መሆኑን አመላክተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG