ዛሬ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ንግግር የሚያደርጉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ገራቸው በሐማስ ላይ ለምታካሂደው ጦርነት የተጠናከረ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ኔታንያሁ በዋሽንግተን ጉብኝት የሚያደርጉት፣ በሐማስ የተያዙ እስራኤላዊ ታጋቾችን እንዲያስለቅቁ በሃገር ውስጥ ከፍተኛ ጫና እየገጠማቸው ባለበት እና ሀገራቸው ዋና አጋሯ ከሆነችው ከአሜሪካ ጋራ የሚኖራት መፃኢ ግንኙነት በኅዳር ወር በሚደረገው ምርጫ ምክንያት ወዴት እንደሚያመራ በማይታወቅበት ሁኔታ ውስጥ ነው።
አሜሪካ፣ ግብፅ እና ካታር በእስራኤልና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለወራት ቢጥሩም ሳይሳካ ቀርቷል። በጋዛ ጦርነቱ እየቀጠለ፣ በሌባኖስ ድንበር ላይ ግጭቱ እየጨመረ፣ እንዲሁም በየመን የሚገኙት የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ በሚመላለሱ መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እያየለ ባለበት ሁኔታ፣ ጦርነቱ ወደ ቀጠናው እንዳይስፋፋ አስግቷል።
ከሁለቱም ፓርቲዎች ድጋፍ እንደሚሹ ኔታንያሁ ተናግረዋል። የኔታንያሁ በዋሽንግተን መገኘት በዲሞክራቶችና በሪፐብሊካኖች መካከል ያለውን ልዩነት ያባባሰ ሲሆን፣ በርካታ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ዓባላት በንግግራቸው ላይ እንደማይታደሙ አስታውቀዋል።
ኔተንያሁን የጋበዟቸው የም/ቤቱ አፈ ጉባኤ ማይክ ጃንሰን፣ የምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ አለመገኘት “ምክንያታዊ”እንዳልሆነ ተናግረዋል። ሐሪስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከመጪው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እጩነት ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ በምርጫ ዘመቻዎች እየተዘዋወሩ ናቸው፡፡
ከዶናልድ ትረምፕ ጎን ሆነው በምክትል ፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት ጄ. ዲ. ቫንስም በኔታንያሁ ንግግር ላይ እንደማይገኙ ታውቋል።
ዲሞክራቱ ሴነተር በርኒ ሳንደርስም በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ላይ እንደማይገኙ አስታውቀው የኔታንያሁን የዌስት ባንክ እና የጋዛ ፖሊሲ ነቅፈዋል፡፡
ሌላው ዲሞክራት ሴኔተር ዲክ ደርባን በበኩላቸው ከእስራኤል ጎን እቆማለሁ፡፡ ነገር ግን የአሁኑን ጠቅላይ ሚንስትሯን ቆሜ በጭብጨባ አላጅብም” ብለዋል፡፡
ነቃፊዎች የኔታንያሁ መንግሥት ጋዛ ውስጥ በሚያካሂደው ጦርነት በተለይም ደግሞ የፍልስጥኤማዊያንን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ሰብዓዊ ረድኤት ያለእክል እንዲገባ በቂ ጥረት አላደረገም የሚል ትችት ያቀርቡበታል፡፡ እስራኤል በበኩሏ ሃማስ ሲቪሎች በሚኖሩባቸው ኣካባባኢዎች እየተንቀሳቀሰ ለአደጋ የሚያጋልጣቸው ሓማስ ነው በማለት ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች፡፡
ትላንት ማክሰኞ በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት እና ኔታንያሁ ባረፉበት ሆቴል ደጃፍ የተቃውሞ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን ለዛሬም በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች የታቀዱ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በዋሽንግተን “ናሺናል ሞል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰልፎች የነበሩ ሲሆን እስካሁኑ ጋዛ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ታጋቾች ቤተሰቦች ኔታንያሁ ታጋቾቹን የሚያስለቅቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል፡፡
መድረክ / ፎረም