ምክትል ፕሬዝደንት ካመላ ሄሪስ ዛሬ ወደ ኢንዲያናፐሊስ ግዛት አቅንተው ‘ዜታ ፊ ቤታ’ በተሰኘው የዩኒቨርስቲና ኮሌጅ ሴት ተማሪዎች ማኅበር (ሶሮሪቲ) ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን አግልለው፣ ካመላ ሄሪስ ፕሬዝደንታዊ እጩ እንዲሆኑ ድጋፋቸው ከገለጹ ወዲህ ከተደረጉ የመጀመሪያ ሕዝባዊ ክንውኖች አንዱ ነው።
‘ዜታ ፊ ቤታ’ በሚል የግሪክ ፊደላት ምጻረ ቃል የሚታወቀው የተማሪዎች ማኅበር፣ በእ.አ.አ 1920 በወቅቱ የሃዋርድ ዩኒቨርስቲ አምስት ሴት ተማሪዎች የተመሠረተ ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዝደንቷም ከዚሁ ዩኒቨርስቲ የተመረቁ ናቸው። በአሜሪካ ከሚገኙ ግዙፍ ጥቁር ሴት ተማሪዎች ማኅበራት አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ማኅበራቱ የትምሕርት ልዕቀት፣ የሥራ ዕድገት፣ የማኅበረሰብ አገልግሎትና ሌሎችንም ተግባራት ይደግፋሉ።
በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ካመላ ሄሪስ ዳላስ፣ ቴክሳስ ላይ 20ሺሕ ለሚሆኑ ‘አልፋ ካፓ አልፋ’ ተብሎ ለሚጠራውና እርሳቸውም ዓባል ለሆኑበት የሃዋርድ ዩኒቨርስቲ የሴት ተማሪዎች ማኅበር ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ባይደን ለሄሪስ ድጋፋቸውን እንደሰጡ፣ “በጥቁር ሴቶች እናሸንፍ” የተሰኘ ቡድን በዙም ባደረገው ስብሰባ፣ 44 ሺሕ ተሳታፊዎች ተገኝተው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ለካመላ ሄሪስ የምርጫ ዘመቻ አዋጥተዋል። በዚህም የሴት ተማሪዎች ማኅበራት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው ተብሏል።
በተመሳሳይ “በጥቁር ወንዶች እናሸንፍ” የተሰኘ ቡድን ደግሞ 1ሚሊዮን ዶላር አሰባስቧል። ባይደን ለምክትል ፕሬዝደንቷ ድጋፋቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ በነበሩት 48 ሰዓታት ውስጥ 100 ሚሊዮን ዶላር ለምርጫ ዘመቻቸውን ተዋጥቷል። ይህም ገንዘብ በተለምዶ የፖለቲካ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሜቴዎች ከሚሰበስቡት ውጪ ሲሆን፣ በእርሳቸው ወገን የሚንቀሳቀሰው ኮሚቴ 150 ሚሊዮን ዶላር ቃል እንደተገባለት አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም